👉 ለሌሎች አሰልጣኞች ተስፋ የፈነጠቁት የወልቂጤው አሰልጣኝ
በፕሪምየር ሊግ ማሰልጠን ለተወሰኑ አሰልጣኞች እንደርስት የተተወ እስኪመስል የተወሰኑ አሰልጣኞች በሊጉ ክለቦች እየተዟዟሩ ማሰልጠን እየተለመደ በመጣበት የሀገራችን ሊግ ወልቂጤ ከተማ በክረምቱ ለሌሎች ክለቦች ፈር ቀዳጅ የሆነ ድፍረት የተሞላበትን ውሳኔ በመወሰን ያልተጠበቀ የአሰልጣኝ ቅጥር አከናውኗል። ከዚህ ቀደም በታችኛው የሊጉ እርከን በማሰልጠንና ጥሩ ኳስን መሰረት ያደረገ ቡድን ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት ይታወቁ የነበሩት የቀድሞው የኢኮሥኮ አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን የመጀመሪያውን በፕሪምየር ሊጉ የማሰልጠን እድል በመስጠት ነበር ወደ ክለባቸው ያመጡት።
አሰልጣኙም በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ኳስ ቁጥጥር ላያ ያተኮረ ቡድን ለመስራት ቢታትሩም በሒደት እንደሁኔታው ተለዋዋጭ በሆነ አጨዋወት መልካም የሚባል ለቡድኖች አጨዋወት አፀፋ የሚሰጥ/reactive/ ቡድን በመገንባት ጥሩ የውድድር ጊዜ እያሳለፉ ይገኛል። ይህም በታችኛውና በላይኛው የሊጉ እርከን በሚገኙ አሰልጣኞች መካከል የአጋጣሚዎች ጉዳይ እንጂ ሌሎች ነጥረው መውጣት የሚችሉ ጠንካራ አሰልጣኞች ስለመኖራቸው በአብነት መጠቀስ የሚችሉ አሰልጣኝ ናቸው።
👉 የወልዋሎ አደናጋሪው የተጫዋቾች የሚና ለውጥና በአሰልጣኙ ዙርያ የነበረው ውዥንብር
በዘንድሮ የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ የሚመሩት (አሁን ከቡድኑ ተለያይተዋል) ወልዋሎ በሊጉ ጥሩ የሚባል የውድድር አመትን ጅማሮ ማድረግ ችለዋል፤ በወቅቱም ከውጤታማነታቸው በስተጀርባ አሰልጣኙ ይከተሉት የነበረው የተጫዋቾችን ሚና የመለዋወጥ ሂደት ከፍተኛ ሙገሳ ሲያስገኝላቸው የነበረ መሆኑን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር።
ተጫዋቾችን በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ከሚፈጠር ድካም መታደግ ዋነኛ መነሾነት አሰልጣኞች ከጨዋታ ጨዋታ ተወዳዳሪ የሆነ ቡድን ይዘው ለመቅረብ ተጫዋቾችን በማፈራረቅ መጠቀም በዘመናዊ እግርኳስ የተለመደ አካሄድ ነው። ከዚህም አለፍ ሲል ጉዳቶች ሲከሰቱ አሰልጣኞች የሚፈጠረውን ክፍተት ለመፍጠር ተጫዋቾችን ከተለመደው የመጫወቻ ቦታዎች እንደ ሁኔታው በአዳዲስ ሚናዎች መጠቀምም (Make Shift) የተለመደ ነው።
በወልዋሎ ግን እየሆነ የሚገኘው ከዚህ በተቃራኒ በቡድኑ ውስጥ ተጠቃሽ የሚባለው በትግራይ ደርቢ በመቐለ በተሸነፉበት ጨዋታ ዓይናለም ኃይለ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ ለሳምንታት ከራቀበት እና አጥቂው ካርሎስ ዳምጠው ከገጠማቸው ጉዳት በዘለለ የሚጠቀስ የቡድኑን መዋቅር የሚያፋልስ ጉዳት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በቀጥታ በሁለቱ ተጫዋቾች ምትክ ቡድኑ ተፈጥሮአዊ የተጫዋቾች አማራጭ አማራጮች ቢኖሩትም የቡድኑ የአሰልጣኞች ቡድን ይህን አማራጭን ግን ለመጠቀም አልፈቀዱም ይልቁንስ የተጫዋቾች የሚና ለውጥ በማድረግ ይህን ክፍተት ለመድፈን ሙከራዎችን ሲያደርጉ ይስተዋላል።
ከዚህኛው ምርጫቸው ጀርባ የተለየ ታክቲካዊ ተልዕኮ ሊኖር እንደሚችል ቢጠረጠርም ሜዳ ላይ ይህን የሚያሳዩ ምልክቶችን ግን በተደጋጋሚ መመልከት አልቻልንም። ይልቁንስ የዚህ ድፍረት የተሞላበት የተጫዋቾች ሚና ለውጥ ተጫዋቾች በቀደመው ቦታቸው ለቡድናቸው ይሰጡ የነበረውን ግልጋሎት ሲገድብባቸውና ቡድኑን ከመጥቀም ጋር አራርቋቸው ተስተውሏል። ለማሳያነትም ሳሙኤል ዮሀንስ ፣ ገናናው ረጋሳ ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና ብሩክ ሰሙ የመሰል ሚና መደበላለቆች እየተጎዱ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው።
ከወልዋሎ ጋር የተያያዘው ሰሞነኛ የመነጋገርያ ርዕስ የአሰልጣኙ እና የክለቡ ግንኙነት ነው። ከቀናት በፊት ሶከር ኢትዮጵያ ከወልዋሎ ስራ አስከያጅ አቶ አሸናፊ አማረ ባገኝችው መረጃ ዋና አሰልጣኙ ዮሐንስ ሳህሌ በቦርዱ ውሳኔ መሰናበታቸው መግለጿ ይታወሳል። ሆኖም ክለቡ ብዙም ሳይቆይ የስራ አመራር ቦርዱ በጉዳዩ ዙርያ ለስብሰባ እንዳልተቀመጠ እና አሰልጣኙም እንዳልተሰናበተ ገልጾ ጉዳዩ አነጋጋሪ መሆኑ የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። ምንም እንኳ ክለቡ ከአሰልጣኙ ጋር ያለውን ነገር ባይለይለትም (ዛሬ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል) ስራ አስከያጁ ለሶከር ኢትዮጵያ ከሰጡት ሀሳብ በኃላ ለተቋማችን መረጃው እንዳልሰጡ እና ዜናው ከእውነት የራቀ መሆኑ በክልሉ የቴሌቭዥን ጣብያ ጨምሮ ለሌሎች መገናኛ ብዙሀን መግለፃቸው ጉዳዩ የእግር ኳስ ማሕበረሰቡን አወዛግቧል።
👉 “ስለዳኝነት አስተያየት መስጠት አልፈለግም ግን……..” የተለመደችው የቅሬታ ማቅረቢያ መግቢያ
ከጨዋታው ውጤት በስተጀርባ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የሴራ ንድፈ ሃሳቦችና የሜዳ ውጭ ሁነቶች በሚቀርቡበት የሀገራችን እግርኳስ በድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቆች ላይ የተሸናፊ ቡድኖች አሰልጣኞች ከሽንፈት መልስ ዳኝነቱ ላይ ጣትን መቀሰር የተለመደ ሂደት እንደሆነ ቀጥሏል። ሁሌም ቢሆን ስለዳኝነቱ መጠየቃቸው የማይቀር ነገር ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ አሰልጣኞችም በአፀፋው ዳኞችን መወረፋቸው የተለመደ እውነታ ከሆነ ሰነባብቷል።
ከእነዚህ በዳኝነት ዙርያ ለሚቀርቡ ሂሶች አብዛኛዎቹ በመግቢያነት ተመሳሳይ ሀረግን ሲጠቀሙ ይስተዋላል “ስለዳኝነት አስተያየት መስጠት አልፈለግም፤ ግን…” በሚል መግቢያ የሚጀመሩት ንግግሮች ሲጠናቀቁ ግን ዳጎስ ያለ የተቃውሞና የትችት ሀሳቦች የሚቀርቡባቸው ሆኖው ይገኛሉ።
👉 በሁኔታዎች ያልተቃኘው የአሸናፊ በቀለ ቅያሬ
በ13ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር አዳማ ከተማ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ በሲዳማ ቡና የ3-2 ሽንፈት አስተናግዶ ተመልሷል። በጨዋታውም በሁለተኛው አጋማሽ እንደተለመደው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ያደረጓቸው ቅያሬዎች ልክ ስለመሆናቸው ጥያቄ የሚነሳባቸው ነበሩ።
ለወትሮም ቢሆን የመሐል አማካዮች ፍቅር በፅኑ የተለከፉ የሚመስሉት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ሶስት ተቀራራቢ ባህሪ ያላቸውን የመሀል አማካዮች ሲጠቀሙ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ደግሞ ሶስት በቋሚነት ከተሰለፉት የመሀል ተጫዋቾች የቀረቡ ተጫዋቾችን መያዛቸው በራሱ አግራሞትን የሚጭር ነበር።
በአንዳንድ የአውሮፓ ታላላቅ ክለቦች እንደሚስተዋለው ፊት ላይ ፈጣንና አስፈሪ የፊት መስመር ጥምረት ያላቸው ቡድኖች የፊት መስመር ተሰላፊዎቻቸው አቅም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በስፋት ለመጠቀም ለማሰብ ከአጥቂዎች በስተጀርባ የስድስት ቁጥርን ሚና መወጣት የሚችሉ ተጫዋቾችን ቁጥር በማብዛት የቡድኑን የመከላከል ሚዛን ለማስጠበቅ ጥረቶች ሲያደርጉ ቢስተዋልም በአዳማ ይህን አካሄድ ለመከተል የሚመስል የወረቀት ላይ የመጀመሪያ ተሰላፊዎች ስብጥር ቢኖርም ከአሰልጣኙ የተጋነነ የመከላከል ሚዛን እሳቤ የተነሳ የአዳማ የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከማጥቃት ነፃነት ባሻገር በመከላከሉም ሀላፊነት ስለሚጣልባቸው አስተሳሰብ በበቂ መልኩ እንዳይተገበር ተግዳሮት ሲሆን ይስተዋላል።
ምንም እንኳን ወሳኙ የፊት አጥቂያቸው ዳዋ ሆቴሳን ሳይዙ ወደ ሀዋሳ አቅንተው ሲዳማን የገጠሙ ቢሆንም እጅግ አዝናኝ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ 3-2 በባለሜዳዎቹ እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል። ከእረፍት መልስ የመስመር ተከላካዮን ሱሌይማን መሐመድን በምኞት ደበበ በመቀየር የመጀመሪያ ቅያሬያቸውን ያደረጉት አሰልጣኙ በመቀጠል በ78 እና 85ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ ፈረጃንና አማኑኤል ጎበናን አስወጥተው ሚካኤል ሳንጋሪና ብሩክ ቃልቦሬን አስገብተዋል። በደፈናው እነዚህ ቅያሬዎች እየተመራ ለሚገኝና ቢያንስ አቻ ለመሆን አንድ ግብ ለሚፈልገው ቡድኑ ይበልጥ የማጥቃት አማራጭን ከመስጠት ይልቅ ከተጫዋቾቹ ባህሪ በመነሳት የቡድኑን የመሀል ለመሀል ጥቃትን የመሰንዘር አቅምን የሚያጠነክሩ ይመስላል።
👉 ቁጥቡ አሰልጣኝ አዲሴ በስተመጨረሻም ደስታቸውን ሲገልፁ ታይተዋል
በደጋፊዎቻቸዎ ዘንድ ከጨዋታ ስልትና ውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ እያስተናገዱ የሚገኙት የሀዋሳ ከተማ አለቃ አዲሴ ካሳ በዚህኛው ሳምንት ተቸግረው ቢሆን ጅማ አባጅፋርን በማሸነፍ ድል ማድረግ ችለዋል።
ለወትሮም ቢሆን ቡድኑ ላይ ስለተፈጠረው ከፍተኛ ጫና ተደጋጋሚ ሀሳቦችን ሲሰነዘሩ የሚደመጡት አሰልጣኙ በዚህኛው ሳምንት ጨዋታ ላይ ለወትሮው ከሚታወቁበት ባህሪ በተቃራኒ ደስታቸውን ሲገልፁ ተመልክተናል። ለወትሮም ቢሆን የተረጋጋ ስብእና ባለቤት የሆኑት አሰልጣኙ በሜዳው ጠርዝ ሲወራጩና ሲቅበጠበጡ የማይታዩ ሲሆን አብዛኞቹን የጨዋታ ደቂቃዎች በተረጋጋ ስሜት ውስጥ ሆነው ከመቀመጫቸው ሳይነሱ የሚያሳልፉ አሰልጣኝ ናቸው። በጅማው ጀዋታ ግን በ74ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ በግሩም አጨራረስ ግብ ካስቆጠረ በኃላ ወደ ተመልካች ዙረው ደስታቸውን ሲገልፁ የተመለከትንበት መንገድ ትኩረት የሳበ ገጠመኝ ነበር።
👉 ዓበይት አስተያየቶች
– ፋሲል ተካልኝ ስለቡድኑ የጨዋታ አቀራረብና የመከላከል ድክመት
“ውድድሩ ሲጀመር የነበረው እና አሁን ያለው ቡድን የተለያየ ነው። አመቱ መጀመሪያ ላይ እንደተመለከታችሁት የተሟላ ቡድን ነበረኝ። በዛም ጊዜ በምንፈልገው መንገድ ነበር ስንጫወት የነበረው። ነገር ግን ከሶስት እና ከአራት ሳምንታት በፊት በርከት ያሉ ተጨዋቾችን በጉዳት እያጣሁ ስለሆነ ለቡድኔ የሚያዋጣውን የጨዋታ መንገድ እያሰብኩ ነው ወደ ሜዳ የገባሁት። ። ነገር ግን በዋናነት የተጨዋቾች ጉዳት የምንፈልገውን የጨዋታ መንገድ እንዳንከተል አድርጎናል። እኔ በተጨዋቾቼ ጠንካራ ጎን ላይ ነው ብዙ ማተኮር የምፈልገው። በእርግጥ ግን በመከላከል ላይ ያለብንን ስህተቶች ማስተካከል ይኖርብናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ወይ በመስራት ችግርክን ትቀርፋለክ ወይንም ደግሞ አዲስ ተጨዋች በማስፈረም ለችግሩ መፍትሄ ትሰጣለክ።”
– አሰስልጣኝ ውበቱ አባተ ስለ ፍፁም ዓለሙ የደስታ አገላለፅ
“በቅድሚያ እንደ ኢትዮጵያዊ እኛ ባህል ያለን ሰዎች ነን። ማንም ቢሆን እንግዳን ማክበር አለበት። ተጨዋቹ ጎሉን ካገባ በኋላ ወደ እኛ መጥቶ አንገቱን እንደ ማረድ ነው ያሳየው። ይህ ደግሞ በጣም ነውር ነው። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዋና ዳኛውም ሆነ ረዳት ዳኞቹ ደስታ አገላለፁን አይተውታል። ነገር ግን በካርድ አልገፀሱትም። እኔ በግሌ ተጨዋቹ በውስጡ ምን እንዳለው አላቅም። የቀድሞ ጥሩ ተጨዋቼ ነበር። አሁንም ጥሩ ተጨዋች ነው። ነገር ግን ለራሱ ይህንን ባለጌ ተግባር ማረም አለበት።”
– ገብረመድህን ኃይሌ ስለተቆጠሩባቸው ግቦችና ተጫዋቾች ሀሳባቸውን ለመተግበር ስለመቸገራቸው
“የመጀመሪያው ግብ ትኩረት የማጣት ችግር ነበር ሁለተኛው እንደዚህ ሙሉ አቅማችንን ተጠቅመን ለማጥቃት በምናደርገበት ወቅት በተገኘ መልሶ ማጥቃት የተገኘ ግብ ነው። የብልጠት ችግር ይታይብን ነበር። የጨዋታ ፍልስፈናየን ያልተገበሩልኝ ተጫዋቾች ነበሩ የፍፁም ቅጣት ምት በምናገኝበት ወቅትም አጋጣሚውን አለመጠቀማችን የፈጠረብን ተፅዕኖ ነበር እሱ እሱ ተደጋጋሚ ስህተት ስለሆነ ደጋግሞ አጋጣሚዎች ያመከንን ስለነበር አማኑኤል ወደ ጨዋታ መመለስ አልቻለም እና ሌሎች ነገርች ተጨማምረው ለሽንፈት ዳርገወናል ግን ቡድናችን በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ አቋም ላይ ነበር ።
– ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስለአዳሱ ቡድናቸው እንቅስቃሴ
“የነጥቡ መራራቅ ምናልባት በልጆቻችን ላይ ጫና እንዳያሳድር ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ለኔ የመጀመሪያ ጨወታ ነው፡፡ ብዙ ስዕል አሳይቶኛል፡፡ አሁን ሁለት ጨዋታዎች ይቀራሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በክፍተቶቻችን ላይ ሰርተን በአብዛኛው በሁለተኛው ዙር ላይ አጠናክረን የምንቀጥልበት ሁኔታ ነው ምናመቻቸው፡፡ በቀሪ ጨዋታዎች ጥሩ ስራ ሰርተን እንታገላለን ብዬ አስባለሁ፡፡እንግዲህ በድክመት ደረጃ እንዲህ ነው ብዬ መለየት አልቻልኩም ለምሳሌ በልምምድ ቦታ እንኳን አስራ አንድ ለአስራአንድ ሆነው ጨዋታ ሲያደርጉም አላየዋቸውም ከስማቸው ጋር ለመላመድም በጣም ጥቂት ቀናቶች ናቸው የነበሩኝ ለኔ ትንሽ ፈታኞች ናቸው ያ ማለት ግን በሂደት ሚስተካከሉ ናቸው በየቦታው ጥራት ያላቸውን ተጫዋቾች አሉ፡፡ የግል ክህሎታቸው ጥሩ የሆኑ ልጆች አሉ እስኳድ አንፃር አሁን ሀያ ተጫዋቾች ናቸው ያሉት አንድ የተጎዳ አለ ሀያ አንድ በቡድኑ ያለው ስለዚህ ቡድኑን የማስፋት ስራን በስፋትም በጥራትም ማስካከል የሚገባን ነገር አለ ብዬ አስባለሁ እና ምናልባት ይሄ ጥራቱ ላይ ቡድኑን ማስፋት እንዳለብን የሚታየኝ ነገር አለ፡፡”
– ካሳዬ አራጌ ስለአማራጭ የጨዋታ እቅድ
” በተጋጣሚ ቡድኖች ጫና ውስጥ ለመውጣት የሞከርንበት መንገድ በረከት አህመድን ለማግኘት የሚሄድበት መንገድ ነበር ይህም የቅብብል ስህተት ነው እንጂ ጥለዛ አልነበረም።ሁለተኛ አማራጭ ለሚባለው ነገር የሰው ለውጥ ያስፈልጋል ፤ ሁለተኛ እቅድ ካስፈለገ ተጫዋቾችን መለወጥ ያስፈልጋል።ግን ለማፈን በሚደረገው ሂደት ውስጥ ለመውጣት በምናረገው ሂደት ውስጥ የቅብብል ስህተቶች ይኖራሉ ፤ እነዛን ደግሞ መታገስ ያስፈልጋል።”
– ሥዩም ከበደ ከሜዳ ውጪ ስለማሸነፍ
“አሁን 12ኛ ጨዋታችን ነው። ከሜዳ ውጭ ያሸነፍነው ጨዋታ የለም። ሁለት ጊዜ ተሸንፈን አራት ጊዜ አቻ ወጥተናል። ሜዳችን ላይ ስድስት ጨዋታ አድርገናል፤ ስድስቱንም አሸንፈናል። ከሜዳ ውጭ ያደረግናቸው ጨዋታዎች ላይ አንዳንዱ ጥሩ የሆነ የተበላሸብን ጨዋታዎች አሉ። ከነዚህም ውስጥ ሰበታ ከነማ እና ጅማ አባጅፋርን መጥቀስ ይቻላል። በዚህም ምክንያት ልጆቼ ላይ ጫና ነበር። ዛሬ ውጤት መያዛችን ትልቅ ነገር ነው፤ ውጤት ስንይዝ ደግሞ ውጤቱንም እየፈራን የደረሰብን ነገር አለ። ሰበታ ላይ አራት ደቂቃ ሲቀር ነው አቻ የወጣነው። ከሽረ ጋር ደግሞ ሰማንያ ስድስታኛ ደቂቃ በኋላ ነው ሁለት ግብ የገባብን። በተመሳሳይ በዚህም ጨዋታ የያዝነውን ውጤት እንዳናጣ በሚል በተጫዋቾች ላይ ትልቅ ጫና ነበር። መቐለዎች በበኩላቸው የሚችሉትን ያህል ሞክራዋል በውስጥም በውጭም እንቅሰቃሴዎች ጥሩ ነበር፤ የሚችሉትን ያህል ጫና አድርገዋል። እኛም ያገኘነውን አስጠብቀን ለመሄድ ጥሩ ነገር አድርገናል። ምክንያቱም ቀሪ ጨዋታ የሚኖረን ሁለት ጨዋታ ነው። ይሄን ሁለት ጨዋታ አንድ በሜዳችን አለን። አንዱ ከሜዳ ውጭ ነው በእነዚህም ጨዋታዎች ወጤት አስጠብቀን መውጣት ማለት ደረጃችን ከፍ አድርገን አንደኛ ዙር መጨረስ እንችላለን። እና በአጠቃላይ ይሄ ጨዋታ ለኛ ትልቅ ውጤት ነው። ደጋፊዎቻችንም እኛ ጋር ብዙ ነገር ይሉ የነበረው ከሜዳ ውጭ ባለን አቋም ነበር። እና ዛሬ ተሳክቶልናል በአጠቃለይ ጥሩ ጨዋታ ነው ብዬ አስባለሁ።”
©ሶከር ኢትዮጵያ