የፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ቁጥሮች እና እውነታዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንትን የተመለከቱ ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎችን በሚከተለው መልኩ አሰናድተናል።

👉 የፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ውጪ ድል

በዚህ ሳምንት ሁለቱ ክለቦች ከሜዳቸው ውጪ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ተመልሰዋል። ይህ ድል ለሁለቱም በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ደደቢትን ካሸነፈ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑ ነው። ፋሲልም ከ9 ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሰ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ከሜዳው ውጪ ያሸነፈው እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉ ደደቢትን መሆኑ ግጥምጥሞሹን አስገራሚ አድርጎታል። 

👉 የመቐለ ሽንፈት

በሜዳው ጠንካራ የሆነው መቐለ 70 እንደርታ በዚህ ሳምንት የደረሰበት ሽንፈት ከስምንት ጨዋታ በኋላ በሜዳው የተከሰተ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ ሽንፈት ያስተናገደው በግንቦት ወር 2011 በሀዋሳ ከተማ ነበር።

👉 ጎሎች በቁጥራዊ መረጃ

– በአስራ ሦስተኛው ሳምንት 23 ጎሎች ተቆጥረዋል። ይህም ባለፈው ሳምንት ከተቆጠረው የጎል ብዛት በአንድ ዝቅ ያለ ነው። 

– በዚህ ሳምንት ጎል ሳያስቆጥሩ የወጡ ቡድኖች ካላፈው ሳምንት በሦስት ቀንሶ 3 ሆኗል። ጅማ፣ ሆሳዕና እና መቐለ ያላስቆጠሩ ቡድኖች ናቸው።

– በዚህ ሳምንት 19 ተጫዋቾች ጎል በማስቆጠር ተሳትፈዋል። ሙጂብ ቃሲም፣ ጌታነህ ከበደ፣ ስንታየሁ መንግሥቱ እና አቤል ያለው ሁለት ጎሎች ማስቆጠር ሲችሉ ቀሪዎቹ 15 ተጫዋቾች አንድ አንድ ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ከተቆጠሩት 23 ጎሎች መካከል 15 ጎሎች በአጥቂ (የመሐል እና የመስመር) ተጫዋቾች ሲቆጠሩ 5 ጎሎች በአማካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። 3 ጎል ከተከላካይ ሥፍራ ተጫዋቾች ተገኝቷል።

– ከ23 ጎሎች መካከል 18 ጎሎች ከክፍት ጨዋታ ሲቆጠሩ 2 ጎል ከማዕዘን ምት ተሻምቶ ተቆጥሯል። አራት ጎሎች ደግሞ ከፍፁም ቅጣት ምት ተቆጥረዋል።

– ከ23 ጎሎች መካከል 20 ጎሎች ሳጥን ውስጥ ተመትተው ሲቆጠሩ 3 ጎሎች ከሳጥን ውጪ ተመትተው ጎል ሆነዋል።

👉 ካርዶች በዚህ ሳምንት

– በዚህ ሳምንት 33 የማስጠንቀቂያ እና 3 የቀይ ካርዶች ተመዘውበታል። 

– ከተመዘዙት የማስጠንቀቂያ ካርዶች መካከል 31 ለተጫዋቾች ሲሆን አንድ ለግብ ጠባቂ አሰልጣኝ፤ አንድ ደግሞ ባልተለመደ ሁኔታ ለወጌሻ (የቅዱስ ጊዮርጊስ) ተሰጥቷል።

– ሲዳማ ቡና ከ አዳማ ያደረጉት ጨዋታ በሁለት የማስጠንቀቂያ ካርዶች ዝቅተኛው ሆኖ ሲመዘገብ ሀዋሳ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር ደግሞ በ6 የማስጠንቀቂያ እና አንድ ቀይ ካርድ ከፍተኛው ሆኖ አልፏል።

– በሊጉ ዝቅተኛው የማስጠንቀቂያ ካርድ የተመዘገበበት ወልዋሎ በዚህ ሳምንት ምንም ካርድ ያልተመከቱ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ6 ከፍተኛው ነው።

👉 በዚህ ሳምንት…

– በዚህ ሳምንት አምስት ተጫዋቾች ዘንድሮ በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ጎል አስቆጥረዋል። ዳዊት ወርቁ (ወልዋሎ)፣ ቡልቻ ሹራ እና ቴዎድሮስ በቀለ (አዳማ ከተማ)፣ ደጉ ደበበ ( ወላይታ ድቻ)፣ ታደለ መንገሻ (ሰበታ ከተማ) ለመጀመርያ ጊዜ ጎል ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።



© ሶከር ኢትዮጵያ

በሶከር ኢትዮጵያ የሚወጡትን ቁጥራዊ መረጃዎች እና እውነታዎች በቀጥታም ሆነ በግብዓትነት ሲጠቀሙ ምንጭ ይጥቀሱ።