የፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት – ዓበይት ጉዳዮች (፬) | ሌሎች ጉዳዮች

👉 ተቃውሞዎች እና ሰጣገባዎች እዚህም እዛም እያቆጠቆጡ መጥተዋል

በ13ኛው ሳምንት በተለያዩ ከተሞች ሲካሄድ በተለይ ዘንድሮ በዓመቱ ጅማሮ ለሀገራችን እግርኳስ ከፍተኛ ስጋት የነበረውና በሒደት ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እያስመለከተን የነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉዳይ ዳግም ማገርሸት መንስኤ የሚሆኑ ክስተቶችን በስፋት ያስመለከተ ሳምንት ነበር።

በዚህ ሳምንት እንኳን ከተደረጉ ጨዋታዎች መካከል በግማሾቹ መሰል አዝማሚያዎችን ተመልክተናል። ለመጥቀስ ያህልም ሲዳማ ቡና አዳማን 3-2 ሲረታ በዳኞች ውሳኔ መዘበራረቅ መነሾ በሁለቱ ቡድን አባላት መካከል በተፈጠረ ሰጣገባ እና የሲዳማ ደጋፊዎች ባነሱት ከፍተኛ ተቃውሞ ጨዋታው ለ13 ያክል ደቂቃ ተቋርጧል።

በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማ ጅማ አባጅፋርን በረታበት ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የጅማ ተጫዋቾችና በተጠባባቂ ወንበር የነበሩ የቡድኑ አባላት ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በማለት በተፈጠረ ንትርክ 3 ተጫዋቾች በተከታታይ ቢጫ ካርድ እስከመመልከት የደረሱበት ሒደትን ተመልክተናል።

በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በተረታበት ጨዋታ አጀማመሩ በክለቡ አመራሮች ላይ ይመስል በነበረውና የመገናኛ ብዙሃን አባላት ላይ ወከባና ድብደባ ድረስ የደረሰው ተቃውሞ፤ በተመሳሳይ በዚሁ ስታዲየም በሜዳው በፋሲል 2-0 የተረታው የመቐለዎች ከፍተኛ ተቃውሞ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ 1-1 ከተለያየበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የተወሰኑ ደጋፊዎች የቡድናቸው ተጫዋቾች ወደ መጓጓዣ አውቶብሳቸው ሲጓዙ የነበረው የማዋከብ ድርጊት ከላይ ለቀረበው ሀሳብ በማሳያነት መቅረብ የሚችሉ ናቸው።

መሰል ድርጊቶች በየሳምንቱ እዚህ እዚያም ሲታዩ የቆዩ ቢሆንም አሁንም ላይ ግን መስመር ለመሳት የተቃረቡ ይመስላል። በቅርቡ በደጋፊዎች ጥምረት የተጀመረው ደጋፊዎችን የማቀራረብ ስራ ተስፋ ሰጪ ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ይህ ተግባር በክለብ ደጋፊዎች መካከል የነበረውን ውጥረት በማርገብ ረገድ የተሻለ ውጤት እያመጣ ቢሆንም በተናጥል የክለቦች ደጋፊ ማህበራት በራሳቸው ደጋፊዎች ላይ ይበልጥ ስራዎችን መስራት የነገ የማይባል የቤት ስራ ስለመሆነ መመልከት ችለናል።

በተመሳሳይ የጨዋታው አወዳዳሪ አካላት በተለይ የጨዋታ ዳኞችን የሚመድቡበትን መንገድ መፈተሽም የሚያስፈልግ ይመስላል፤ ዳኞች የጨዋታዎችን ክብደት በጥልቀት በመመርመር የተሻለ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችሉ ዳኞችን በመመደብ ለዚህ ጉዳይ መነሾ የሆነውን ደካማ የህግ አተረጓጓመና የተግባቦት ችግሮችን ስለመቅረፍ በደንብ ማጤን ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም ደጋፊዎች ከስሜት በመውጣት ለክለባቸው ሽንፈት የመስዋት በግ ከመፈለግ ይልቅ ስለቡድኖቻቸው አጠቃላይ ቆመና ማጤን ይገባቸዋል።

👉 እክሎች የበዙበት ዘመናዊው የትኬት አሻሻጥ ስርዓት

ለሀገራችን አዲስ የሆነው ዘመናዊ የጨዋታ ትኬት ሽያጭ ስርዓት አሁንም የአተገባበር ችግሮች መታየታቸውን ቀጥለዋል። የደጋፊዎችን እንግልት በማስቀረት ረገድ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ያሳየው የዘመናዊ ትኬት አሻሻጭ ስርዓቱ በተከታታይ የጨዋታ ሳምንታት በሚፈጠሩ የአሰራር መዘበራረቆች ደጋፊዎችን ለእንግልት መዳረጉን ቀጥሏል።

በዚህኛው ሳምንት በአዲስአበባ ስታዲየም ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በተለይ ለእንግዶቹ ወልቂጤ ከተማዎች ሁለቱ የአዲስአበባ ከተማ ክለቦች በተናጥል ጨዋታ ሲያደርጉ እንደሚያደርጉት ከማን አንሼ ባለወንበርና ያለወንበር ያሉት ቦታዎች ለመቀመጫነት የተመደበላቸው ቢሆንም በስታዲየሙ ጨዋታውን ለመታደም ከገቡት ደጋፊዎች የማይተናነስ ቁጥር ያለው ደጋፊ ወደ ቤቱ ለመመለስ ተገዷል።

ከወልቂጤ ደጋፊዎች ማህበር እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ወደ 7 ሺህ የሚጠጋ ተመልካች ጨዋታውን ለመከታተል ትኬት የገዛ ቢሆንም የተመደበላቸው የመቀመጫ የመያዝ አቅም በውል ሳይታወቅ በርካታ ደጋፊዎቻቸው ትኬት ገዝተው ወደ ሜዳ መግባት አልቻሉም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

እንደሚታወቀው የትኛውም አዲስ አሰራር ወደ ተግባር በሚገባበት ሒደት ከአተገባበር ጋር የተያያዙ ግርታዎች የሚጠበቁ መሆናቸው ከስታዲየሙ ወንበር አልባ መሆን ጋር ተያይዞ የስታዲየሙ የመያዝ አቅም በውል ካለመተዋወቅ ጋር ተዳምሮ ለአዲሱ የትኬት ስርአት ተግዳሮት እንደሚሆኑ የሚታመን ቢሆንም ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ወደ ስታዲየም የሚመጡ የየትኛውም ክለብ ደጋፊዎች በአግባቡና ለእንግልት ሳይዳረጉ መስተናገዳቸው ነገር ግን ለድርድር መቅረብ የሌለበት ጉዳይ ነው።

👉 ችላ የተባለው የሀዋሳ ስታዲየም ጉዳይ

በሊጉ ረዘም ላሉ ዓመታት የሊጉን ውድድር በማስተናገድ አንጋፋ ከሚሰኙ ሜዳዎች አንዱ የሆነው ሀዋሳ ስታዲየም አሁን ላይ በጊዜ ሂደት እየጨመረ የመጣውን የስታዲየም ገቢ ደጋፊዎችን ቁጥር ለማስተናገድ እየተቸገረ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ለመታዘብ ችለናል።

በ13ኛ ሳምንት ሜዳቸው በመቀጣቱ የተነሳ በተለዋጭነት ባቀረቡት የሀዋሳ ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ወላይታ ድቻን በጋበዙበት ጨዋታ ስታዲየሙ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ በማስተናገዱ የተነሳ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ተመልካች በስታዲየሙ ዙርያ በሚገኙ መኖርያ ቤቶችና ዛፎች ላይ ሆኖ ለመከታተል ተገዷል። በዚህም በስታዲየሙ አንደኛው ወገን የሚገኝ ዛፍ በመገንደሱ በርከት ያሉ ሰዎች ከዛፉ ላይ መውደቅ መጠነኛ ጉዳት አስተናግደዋል።

ይህ ሁነት በተለይ ሲዳማ ቡና በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሲደጋገም በስፋት የሚስተዋለው ይህ ሂደት አሁንም ሰሚ ያጣ ይመስላል ፤ በከተማው አዲስ የተገነባ ግዙፍ ዘመናዊ ስታዲየም ቢገኝም እድሳት በሚል ምክንያት አገልግሎት መስጠት ካቆመ ሰነባብቷል።

የሀዋሳ ስታዲየም የመያዝ አቅሙን ለማሻሻል ስራዎች መስራት ካልተቻለ በዚህ አካሄድ ለመዝለቅ የሚቸገር ይመስላል።

👉 ዘና የሚሉት ኳስ አቀባዮች ጉዳይ

በፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ወቅት በተለይ ባለሜዳ ቡድኖች ጨዋታውን እየመሩ ሲሆን በኳስ አቀባዮች በኩል ኳስን ለማዘግየት የሚደረጉ ጥረቶችን መመልከት እንግዳ ጉዳይ አይደለም። በዚህኛው ሳምንት በሀዋሳ ስታዲየም ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ ሲጫወት የሆነው ነገር ግን ለየት ያለ ነበር ፤ በጨዋታው ወቅት ኳስን ለማቀበል የተመደቡት ታዳጊ ህፃናት ከተመደቡበት ዋነኛ ስራ ውጭ በሜዳ ላይ ተንጋለው ጨዋታን ሲመለከቱ የተስተዋለ ሲሆን በዚህም ሂደት ኳሶችን ዳግም ለማምጣት ረዘም ያለ ጊዜ ሲወስድባቸው ተስተውሏል። ይህም መስተካከል ያለበትና ለአልተፈለጉ ድርጊቶች ሊጋብዝ የሚችል በመሆኑ መስተካከል ይገባል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ