ከቀናት በፊት ከአሰልጣኝ ከዮሐንስ ሳህሌ ጋር የተለያዩት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎች በምትካቸው ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን በዋና አሰልጣኝነት ለመቅጠር ከጫፍ ደርሰዋል።
ከ2011 የውድድር ዘመን አጋማሽ ወልዋሎን የተረከቡት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በዚህ ሳምንት ከክለቡ ጋር መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን በምትካቸው ዋና አሰልጣኝ በማፈላለግ ያለፉትን ቀናት ያሳለፈው ወልዋሎ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስን ምርጫው አድርጓል።
በ2011 የውድድር ዘመን አጋማሽ ከጅማ አባጅፋር ጋር ከተለያዩ በኋላ ያለሥራ የከረሙት የቀድሞ የፋሲል ከነማ እና ወልዲያ አሰልጣኝ አሰልጣኙ ጫፍ የደረሰውን ድርድር አጠናቀው ወልዋሎን በይፋ የሚረከቡ ከሆነ በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ የሚገኙት ወልዋሎዎችን ከወቅታዊ የውጤት ቀውስ አላቀው በሊጉ የማቆየት የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።
ቡድኑ ነገ በ14ኛ ሳምንት ከሜዳው ውጪ አዳማ ከተማን በምክትል አሰልጣኞቹ እየተመራ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ሲጠበቅ በ15ኛ ሳምንት ከአንን ዓመት በኋላ ወደ ሜዳቸው ተመልሰው ወልቂጤን በሚያስተናግዱበት ጨዋታ ላይ ምናልባትም ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በይፋ ሥራቸውን ተረክበው ቡድኑን እንደሚመሩ ይጠበቃል።
© ሶከር ኢትዮጵያ