የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 5-1 ሀዋሳ ከተማ

መቐለዎች ሀዋሳ ከተማን በሰፊ የጎል ልዩነት ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

“ከመሪዎቹ ብዙም አልራቅንም፤ ካሁን በኋላ የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ግን ወሳኝነት አላቸው” ጎይቶም ኃይለ (የመቐለ 70 እንደርታ ምክትል አሰልጣኝ)

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ለኛ ወሳኝ ነበር። ከሽንፈት ስለመጣን የግድ ማሸነፍ ነበረብን። ጨዋታውን አሸንፈን ወጥተናል፤ በውጤቱም ደስተኞች ነን።

ስለ ተጫዋቾቻቸው ጥሩ መነሳሳት

ተጫዋቾቻችን ላይ የነበረው መነሳሳት በጣም ጥሩ ነበር። በጥሩ ፍላጎት ነበር የተጫወቱት። የአሰልጣኞች ቡድናችንም ሳምንቱን ሙሉ በጥሩ መንገድ ነበር ለጨዋታው ያዘጋጀናቸው። በአጠቃላይ ውጤቱ ጥሩ ነው።

ስለ ሁለተኛው ዙር እቅዳቸው

አንደኛው ዙር እየተገባደደ ነው። ለሁለተኛው ዙር ደግሞ ጠንክረን ነው የምንቀርበው። ከመሪዎቹ ብዙም አልራቅንም፤ ካሁን በኃላ የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ግን ወሳኝነት አላቸው።

“የሚገባቸውን ውጤት ነው ያስመዘገቡት” አዲሴ ካሣ (ሀዋሳ ከተማ)
ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ከጠበቅነው በላይ ነው። ይሄን አልነበረም ያጠበቅነው። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ልንቆጣጠረው ነበር ሀሳባችን ግን አልሆነም። በአስር ደቂቃ ውስጥ ሁለት ግቦች አግብተውብናል፤ ያን ደሞ አነሳስቷቸዋል። ተጫዋች በቀይ ካርድ መውጣቱም የበላይነቱን እንዲወስዱ አስችሏቸዋል፤ ግን ጥሩ ነበሩ። እነሱ በሁሉም መልክ የሚገባቸውን ውጤት ነው ያስመዘገቡት።

ስለ ቡድናቸው ጉዞ

ውጪ ስንወጣ ያለን ነገር እያስጠበቅን አይደለም። እኛ ሰው ሰራሽ ሳር ላይ ነው የምንጫወተው። እዚ ተፈጥሯዊ ሜዳ ስንመጣ እየተቸገርን ነው። በአጠቃላይ ግን በዛሬው ጨዋታ የምናቀርበው ምክንያት የለም። መቐለ የበላይነቱን ወስዷል። ግን የመሀል ተጫዋች ማጣታችንም በጣም ጎድቶናል። (እሱ እያለም ሁለት ግብ ቢያገቡብንም) ትኩረታቸው ማሸነፍ ላይ ብቻ ነበር። እሱንም ከመጀመርያው ነው ያሳኩት።

ስለ ቀይ ካርዱ 

እሱ የዳኛው ውሳኔ ነው። ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ምን እንደሚል አይታወቅም። ግን ሊታገሰው ይገባ ነበር። ሁለት ጎል ገብቶብናል፤ መቐለም እያጠቃን ነበር። ተጫዋቹ የሚያደርገውን አያውቅም፤ እሱም መታገስ ነበረበት።


© ሶከር ኢትዮጵያ