በክለቡ ወቅታዊ አቋም የተደናገጡት የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ አመራሮች ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገዋል።
በርከት ባሉ አጀንዳዎች ላይ ያተኮረው የዛሬው የቦርድ ስብሰባ በዋናነት የክለቡ ወቅታዊ አቋም ጉዳይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል። የውጤት ማጣቱ ምክንያት ምን እንደሆነ እና መፍትሔው ላይ ባተኮረው በዚህ ስብሰባ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ክለቡን እንደማይመጥን እና አሳሳቢ እንደሆነ፤ ኢትዮጵያ ቡና ስለሆነ አይወርድም ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል አፅኖት የሰጠው ስብሰባው “በመጀመርያው ዙር ላይ በነበሩ ክፍተቶች ዙርያ ተነጋግረን የማናስተካክል ከሆነ ጊዜው ከሄደ በኋላ ብንፀፀት ትርጉም የለውም። ይሄ ሁሉ ደጋፊ እና ህዝብ የሚያለቅስበት ሁኔታ ሊፈጠር አይገባም።” የሚል ጠቅለል ያለ ሀሳብ ተነስቶበታል።
በውይይቱ ላይ አሰልጣኝ ካሳዬን ማሰናበት መፍትሔ እንዳልሆነና ይልቁንም በ1995 የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እና የአሁኑ ዘመን ሁኔታ አንድ እንዳልሆነ በማስረዳት እና በማገዝ ዘንድሮ ቡድኑ በሊጉ የሚቆይበትን ድጋፍ በማድረግ በቀጣይ ራሱን እያየ እንዲያስተካከል የሚሉ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን ለቡድኑ ቀጣይ ውጤት ማማር ሁሉም ከክለቡ ጎን እንዲቆም ሁሉም በየዘርፉ የሚጠበቅበትን እንዲሰራ መነጋገራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
©ሶከር ኢትዮጵያ