የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል። በዚህም ወላይታ ድቻ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ መድን፣ አዳማ እና ጊዮርጊስም አሸንፈዋል።

ምድብ ሀ

ሶዶ ስታዲየም ላይ የተደረገው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሲዳማ ቡናዎች ኳስ ተቆጣጥረው በመጫወት ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በረጃጅም ኳሶች ለይ ያተኮረ ጨዋታ ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ብዙም ሙከራ ያልታየበት ጨዋታ ነበር።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገው ጨዋታው በተጀመረ በ4ኛ ደቂቃ ለይ በሲዳማ ቡና በተክላይ ግርማ ነበር። ይህች ሙከራ ለሲዳማ ቡናዎች የመጀመሪያ አጋማሽ ለይ የተደረገች ብቸኛ ሙከራ ነች። 20ኛ ደቂቃ ላይ ቢንያም አበበ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ አበባየሁ አጪሶ በግምባሩ ገጭቶት የግቡ ቋሚ የመለሰበት በድቻ በኩል ቀዳሚው ሙከራ ሲሆች በ32ኛ ደቂቃ አስናቀ አምታታው ከመስመር ለይ ያሻገረውን ኳስ በጥሩ አቋቀም ላይ የነበረው አበባየሁ አጪሶ በግምባር ገጭቶ የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። በጨዋታው ጥሩ ጥሩ የጎል እድሎች ሲያገኝ የነበረው አበባየሁ በ42ኛው ደቂቃም ከምስክር መለሰ የተሻገረለትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ቢመታውም የሲዳማው ተከላካይ መኳንንት መርመራ ደርሶ ከመስመር ለይ አውጥቶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽም ሲዳማ ቡናዎች ኳስን ይዞ በመጫወት ጥሩ ቢንቀሳቀሱም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ አንድ የግብ ሙከራ ብቻ ነው ማድረግ የቻሉት። በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በረጃጅም ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል። በ63ኛ ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አማኑኤል ኦሊሶ ከመስመር ለይ ያሻገረውን ኳስ አበባየሁ አጪሶ በደረቱ አሳርፎ የመታውን ግብ ጠባቂው ሲመልስበት የመጣችውን ኳስ ታምራት ስላስ በድጋሚ ሲሞክረው በጎሉ አናት ለይ ወጥቶበታል። 83ኛ ደቂቃ ደግሞ አበባየሁ አጪሶ ለአጥቂው ታምራት ስላስ በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ ሐብታሙ መርመራ ከግብ ክልሉ በመውጣት በእጅ በመንካቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

የአጋማሹ የሲዳማ ብቸኛ ግልፅ የጎል ዕድል የተፈጠረው በ87ኛ ደቂቃ ሲሆን ዮናስ ኤኔሳ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ይስሀቅ ከኖ አልተጠቀመውም እንጂ ሲዳማዎችን አቻ ለማድረግ የተቃረበ ነበር። ጨዋታውም በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠረችው ብቸኛ ጎል በድቻ 1-0 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።

በምድቡ ሌሎች ጨዋታዎች ወደ አሰላ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 2-1 አሸንፎ የዓመቱን የመጀመርያ ድል አሳክቷል። በረከት ማኅተቤ እና አቤል አዱኛ የፈረሰኞቹን ጎሎች ሲያስቆጥሩ ዳንኤል አብርሃም የጥሩነሽን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።

መከላከያ ከኢ/ወ/ስ/ አካዳሚ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ሲጠናቀቅ ድሬደዋ ከተማ ከ ከኢትዮጵያ ቡና ወደ ሌላ ጊዜ ተሻግሯል።

ምድብ ለ

ባለፈው ሳምንት አራፊ የነበረው ኢትዮጵያ መድን በሜዳው ሀላባ ከተማን ገጥሞ 5-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል። ጌታሁን ካሕሳይ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር፣ ናትናኤል ዳንኤል፣ ናትናኤል እንዳዘዘው እና አብርሃም ብርሀኑ ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥሯል።

አዳማ ከተማ በሜዳው አዲስ አበባ ከተማን አስተናግዶ 3-1 አሸንፏል። የዓምናው ከ17 ዓመት በታች ውድድር ኮከብ ፍራኦል ጫላ፣ ነቢል ኑሪ እና ሙዓዝ ሙኅዲን የአዳማን ጎሎች ሲያስቆጥር ዋሲሁን ዓለማየሁ የአአ ከተማ ጎል ባለቤት ነው።

ወልቂጤ ከተማ በሜዳው ሱሉልታ ከተማን በበረከት ጌቱ እና በረከት አየነው ጎሎች 2-1 ሲያሸንፍ ፋሲል ከነማ ከ አሰላ ኅብረት ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ