በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሦስት መርሀ ግብሮች ሲደረጉበት ንግድ ባንክ አርባምንጭን፣ ሀዋሳም አዲስ አበባ ከተማ ከተማን 8ለ0 አሸንፈዋል፡፡ ድሬዳዋ ደግሞ በሜዳው መቐለን 2ለ0 ድል አድርጓል፡፡
9:00 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲኤምሲ በሚገኘው ሜዳው አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ ከፍፁም የጨዋታ ብልጫ ጋር የግብ ናዳ አዝንቦ 8ለ0 አሸንፏል፡፡ በ15ኛው ደቂቃ ላይ በብርቱካን ገብረክርስቶስ ግብ መሪ መሆን ሲችሉ ረሂማ ዘርጋው አራቱን፣ ሽታዬ ሲሳይ ደግሞ ሦስት ግቦችን አስቆጥራ ጨዋታውም በንግድ ባንክ 8-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ሀዋሳ ላይ በተመሳሳይ 9:00 አዲስ አበባ ከተማን በሜዳው የጋበዘው ሀዋሳ ከተማ እንደ ንግድ ባንክ ሁሉ በአጥቂዋ መሳይ ተመስገን አስደናቂ ብቃት ታግዞ 8ለ0 ረምርሟል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ረገድ እምብዛም በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች መሳይ ተመስገን የግል ጥረቷን በመጠቀም ከምታሳየው ብቃቷ ውጪ የለዘዘ የጨዋታን እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ በአንፃሩ የተገደበ እና በመከላከሉ ብቻ ራሳቸውን አውለው ታይተዋል፡፡ 4ኛው ደቂቃ በግራ በኩል ካሰች ፍሰሀ የሰጠቻትን ኳስ መሳይ ተመስገን ሁለት ጊዜ ወደ ሳጥኑ ገፋ አድርጋ ከገባች በኃላ ሀዋሳን መሪ ያደረገች ግብ ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ግብ ለማስተናገድ የተገደዱት የመዲናይቱ ክለብ አዲስ አበባ ከተማዎች ፍፁም የመከላከል አደረጃጀት እና የቅብብል ስህተት ተጨማሪ ግብ እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡
በነፃነት መና እና መሳይ ተመስገን ጥምረት ወደ ተጋጣሚው ግብ ክልል ለመድረስ ያልተቸገረው ሀዋሳ 10ኛው ደቂቃ በመሳይ ተመስገን አማካኝነት ሁለተኛውን ግብ አገግኝተዋል፡፡ ሁለት ግቦችን ገና በጊዜ ለማስተናገድ የተገደዱት አዲስ አበባ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት አጥቂዎቹ አስራት አለሙ እና ስንታየው ማቲዮስ ካደረጉት የማጥቃት ሁለት ዕድሎች ውጪ ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል መጠጋት ተስኗቸዋል፡፡ በዚህም አጥቂዋ አስራት በግል ጥረቷ በቀኝ በኩል ያገኘችውን ወደ ግብ መትታ ዓባይነሽ የያዘችባት እና የሀዋሳ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ ስህተትን ተጠቅማ ስንታየው ያገኘቻትን ኳስ ወደ ግብ መታ ለጥቂት ከወጣችበት ውጪ ሌላ ተጨማሪ ዕድል ማግኘት አልቻሉም፡፡
29ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ከተማዋ የቀኝ መስመር ተከላካይ መልካም ተፈራ የሀዋሳን አጥቂ ነፃነት መናን በመማታቷ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች፡፡ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጨረስ የተገደደው አዲስ አበባ ከተማ 34ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ከመሀል ሜዳው እየገፋች ወደ ግብ ክልል አምርታ ማራኪ ግብ በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርታለች፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ምስር ኢብራሂም ተጨማሪ ግብ አክላ ሀዋሳ 4ለ0 እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ በእንቅስቃሴ ሊያምር ያልቻለው እና በግብ ግን የታጀበው ጨዋታ በተመሳሳይ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የቀጠለ ነበረ፡፡ እንግዳው ቡድን ከማጥቃት ይልቅ ግቦች እንዳይበዙበት በመከላከል የተጠመደበት እና መሳይ ተመስገን በነገሰችበት ሁለተኛ አጋማሽ ገና በጊዜ ተደጋጋሚ ሙከራን ማድረግ ከቻሉ በኃላ 62ኛው ደቂቃ መሳይ ተመስገን ከካሰች ፍሰሀ ያገኘቻትን ቆንጆ ኳስ ወደ ግብነት ለውጣ የግብ መጠኗን ወደ አራት ከፍ አድርጋለች፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ሀዋሳዎች ሁለት ደቂቃ እንደተቆጠረ ብቻ አይናለም ከቀኝ በኩል በረጅሙ የሰጠቻትን በደረቷ ካበረደች በኃላ ነፃነት መና ወደ ግብነት ለውጣለች፡፡ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት እጅግ ማራኪ ጎል መሳይ ተመስገን አክላ ለራሷ ስድስተኛ ለሀዋሳ ደግሞ ስምንተኛ የሆነች ግብ በማስቆጠር ጨዋታው 8ለ0 ተደምድሟል፡፡ ሀዋሳዎች ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም ሰዓት ተጠናቋል በማለት የእለቱ ዳኛ ግቧን ሽራታለች፡፡
በሌላው ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ መቐለ 70 እንደርታን ገጥሞ 2ለ0 አሸንፏል፡፡ ለድሬዳዋ ግቦቹን ቤተልሄም አሰፋ እና ተከላካዩዋ ሀሳቤ ሙሶ አስቆጥረዋል፡፡
የማክሰኞ መርሐ ግብር
አቃቂ ከ ጌዲኦ ዲላ 9:00 አ/አ ስታዲየም
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መከላከያ 11:00 አ/አ ስታዲየም
© ሶከር ኢትዮጵያ