ከወር በፊት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አንዋር ሜዴይሮ ሴልታ ቪጎን ለቆ ባርሴሎናን መቀላቀሉን አስነብበናችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አንዋር ሜዴይሮ የባርሴሎና ታዳጊ ቡድን (CADETE B) በይፋ የተቀላቀለ ሲሆን ዝውውሩም በስፔን እግርኳስ ፌዴሬሽን እውቅና አግኝቷል፡፡ ነገር ግን የ13 አመቱ ታዳጊ ወደ ላሜስያ ያደረገው ዝውውር በሁለቱ ክለቦች መካከል ቅራኔን የፈጠረ ሲሆን ባርሴሎና በጥብቅ ሲፈልገው በቆየው የሴልታ ቪጎው ኮከብ ኖሊቶ ዝውውር ላይም እክል ፈጥሮበታል፡፡ ለባለፈው አመት በፈጸመው ያልተገባ ዝውውር ምክንያት በፊፋ ሁለት የዝውውር መስኮቶች ተጫዋች እንዳያዘዋውር ታግዶ የነበረው ባርሴሎና አሁንም ሌላ ውዝግብ ውስጥ ገብቷል፡፡
በስፔን ፕሪሜራ ሊጋ ሴልታ ቪጎ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ ካምፕ ኑ ተጉዞ የ6-1 ሽንፈት ሲደርስበት በጨዋታው ላይ የሊዮኔል ሜሲ የፍፁም ቅጣት ምት ለሉዊስ ሱዋሬዝ ማቀበል የአለማችን በርካታ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ቢስብም የሴልታ ቪጎው ፕሬዝዳንት በአንዋር ሜዴይሮ ዝውውር የተሰማቸውን ብስጭት ለመግለፅ በካምፕ ኑ የፕሬዝዳንቶች መቀመጫ ስፍራ ላይ ሳይገኙ መቅረታቸው የስፔኖቹ ተነባቢ ጋዜጦች ማርካ እና አስ ትኩረትን ስቧል፡፡
ሴልታ ቪጎዎች በተጫዋቹ ላይ ያፈሰሱትን ኢንቬስትመንት የሚያካክስ ገንዘብ ባርሴሎና ሳይከፍል የተጫዋቹን መኖርያ ከ1 አመት እድሜው ጀምሮ ከቆየባት የጋላሲያኗ ከተማ ቪጎ ወደ ባርሴሎና እንዳዞረው ይከሳሉ፡፡ ‹‹ የተጫዋቹ እድሜ ዝውውር ለማድረግ እንዳልደረሰ ብንናገርም የካታላኑ ክለብ ችላ ብሎ ትኩረቱን ሌላው ኮከባችን ኖሊቶን መንጠቅ ላይ አድርጓል›› ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
በጃንዋሪ የዝውውር መስኮት ሴልታ ቪጎን ለቆ አሳዳጊ ክለቡ ባርሴሎናን እንደሚቀላቀል ሲጠበቅ የነበረው ኖሊቶ በሁለቱ ክለቦች መሃል በገባው ንፋስ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ‹‹ በሁለቱ ክለቦች መካከል ለአመታት ዘለቀ ጥሩ ግንኙነት ነበር፡፡ አሁን ግን ባርሴሎና በአንዋር ‹‹ስርቆት›› በሰራው ‹‹ሀጥያት›› ምክንያት ሴልታ ቪጎ ለኖሊቶ ዝውውር የሴንቲ ሜትር ያህል ርቀት የሚጓዝበት ምክንያት የለም›› ሲል ሴልታ ቪጎ ልሳን ፅፏል፡፡
አንዋር ለባርሴሎና ለመፈረም ከስምምነት ላይ የደረሰው በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ወቅት ሲሆን በፊፋ የሁለት የዝውውር መስኮቶች እገዳ በተጣለበት ወቅት ለማስፈረም ከተስማማቸው 77 ተጫዋቾች (በሁሉም የእድሜ እርከኖች) አንዱ ነው፡፡ ተጫዋቹ እድሜው የሚፈቅደው በህጻናት ምድብ ውስጥ እንዲካተት ቢሆንም ባርሴሎና ባለክህሎቱን አጥቂ ከወዲሁ እድሜያቸው ከ16 አመት በታች ባሉ ታዳጊዎች ቡድን ውስጥ አካቶታል፡፡ በዚህ ሳምንት እሁድ ባርሴሎና ከሳንታ ጋብሬል ጋር ባደረገው ጨዋታ 4-0 ሲረታ አንዋር ጥሩ እንቅስቃሴ ከማሳየቱ በተጨማሪ አንዷን ግብ ከመረብ ማሳረፍ ችሏል፡፡

እ.ኤ.አ ማርች 3 ቀን 2002 በአዲስ አበባ የተወለደው አንዋር ሜዴይሮ ሮድሪጌዝ በጋላስያን ግዛት በሚኖሩ ስፔናዊያን ቤተሰቦች በማደጎነት የተወሰደው ገና አንድ አመት ሳይሞላው ነበር፡፡ በህጻናት ቡድኖች ውድድሮች እና በአለም አቀፍ የህጻናት ውድድር ባሳየው እንቅስቃሴ የተደመሙት ሴልታ ቪጎዎች በጁላይ 2013 ወደ አካዳሚያቸው ሲቀላቀሉት ባለፈው የውድድር ዘመን በእድሜ እርከናቸው የዋንጫ ባለቤት ሲሆኑ ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይቶ ወደ ታላቁ ክለብ ባርሴሎና ዝነኛ የማሰልጠኛ ማዕከል ‹‹ላ ሜሲያ›› አምርቷል፡፡