ሪፖርት | አዳማ ወልዋሎን በመርታት ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ፈቀቅ ብሏል

በዕኩል 15 ነጥቦች ላይ የነበሩት አዳማ ከተማ እና ወልዋሎ ዓ /ዩን ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ በ13ኛው ሳምንት በሲዳማ ከደረሰበት ሽንፈት ደረጀ ዓለሙ ፣ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ሱለይማን መሐመድ እና ሚካኤል ጆርጅን በጃኮ ፔንዜ ፣ ምኞት ደበበ ፣ ከነዓን ማርክነህ እና ዳዋ ሆቴሳ ለውጦ ለጨዋታው ቀርቧል። በዕንግዶቹ ወልዋሎዎች በኩል በቅዱስ ጊዮርጊሱ ሽንፈት ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አቼምፖንግ አሞስ እና ብሩክ ሰሙን አሳርፈው ለዘሪሁን ብርሀኑ እና ጠዓመ ወ/ኪሮስ የመሰለፍ ዕድል ሰጥተዋል።

ጨዋታው በባለሜዳዎቹ አዳማዎች ፈጣን ጥቃት የጀመረ ነበር። ገና በአንደኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ለቡልቻ ሹራ ያሻገረውን ኳስ ቡልቻ ለመጭረፍ ሲሞክር አብዱላዚዝ ኬይታ ያወጣበት ሲሆን ከአንድ ደቂቃ በኋላም ዳዋ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ አጥብቦ የሞከረውን ኳስም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። መሀል ሜዳ ላይ እምብዛም ያልተቸጉሩት አዳማዎች በቀላሉ የኳስ ቁጥጥሩን በበላይነት መያዝ የቻሉ ሲሆን ወልዋሎዎች በበኩላቸው የቀኝ መስመር አጥቂያቸው ኢታሙና ኬይሙኒ እና ጁኒያስ ናንጂቡን መዳረሻ ካደረጉ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውለዋል። በዚህም 12ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ጠዓመ ወ/ ኪሮስ በጣለለት ኳስ ኢታሙና ከጃኮ ፔንዜ ጋር የመገናኘት ዕድል ቢያገኝም አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

አዳማዎች ምንም እንኳን ኳስ ይዘው በወልዋሎ ሜዳ ላይ ሲቆዩ ቢታዩም ይበልጥ አስፈሪ ይሆኑ የነበረው ወደ መስመር ከሚጥሏቸው ድንገተኛ ኳሶች መነሻነት እና መሀል ለመሀል በድንገት ከሚከፍቷቸው ጥቃቶች ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከመሀል ለከነዓን ማርክነህ አቀብሎት አማካዩ በቀኝ መስመር ገብቶ ሞክሮ የወጣበት ኳስም በዚህ ውስጥ የሚጠቃላል ነበር። ሆኖም ቡድኑ 23ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል በድንገት የከፈተው ጥቃት ወደ ሳጥን አምርቶ በበረከት አማካይነት ወደ ውስጥ ሲላክ በአማኑኤል ጎበና ጨራሽነት ወደ መጀመሪያ ግብነት ሊቀየር ችሏል። 

በአንፃሩ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የነበራቸው ወልዋሎዎች በኩል በ29ኛው ደቂቃ ኢታሙና በረጅሙ በተላከለትን ኳስ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ቢያገኙም ተጨዋቹ ከርቀት ሞክሮ አምክኖታል ፤ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ናሚቢያዊው አጥቂ ከቀኝ በኩል በድጋሚ ባገኘው ዕድል ሳጥን ውስጥ ለነበረው ናንጂቡ ጥሩ ኳስ ቢያቀብልም ምኞት ደበበ ደርሶ አስጥሎታል። አዳማዎች በሰጡት ፈጣን ምላሽም የበረከት የሳጥን ውጪ የቀጥታ ሙከራ ግብ እንዳይሆን የአብዱላዚዝ ኬይታን የመጨረሻ ጥረት የጠየቀ ነበር።

የወልዋሎ ሁለቱ አጥቂዎች ጥምረት በራሱ ፍሬ ባያፈራም የኬይሙኒ ጫና የበረታበት ፉአድ ፈረጃን በሱለይማን መሀመድ ለመቀየር ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መነሻ የሆነ ይመስላል። ሱለይማንም ፉአድን ቀይሮ በገባበት ቅፅበት ከግራ መስመር ያሻማው ኳስ በቀኝ በኩል በሱለይማን ሰሚድ ተሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቷል። በመጨተሻዎቹ ደቂቃዎችም የአዳማን የግራ መስመር የበረታ ግን ደግሞ በጠንካራ ሙከራዎች ያልታጀበ ጥቃት እና የወልዋሎን ወጣ ገባ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የመጀመሪያ አጋማሽ በአዳማ መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተሰነዘሩ ጥቃቶች የጀመረ ነበር። 48ኛው ደቂቅ ላይ በረከት ከዳዋ የተቀበለውን ኳስ አክርሮ ሞክሮ በግብ ጠባቂው ሲመለስበት የ51ኛው ደቂቃ የሄኖክ መርሹ ቅጣት ምት በገናናው ረጋሳ በግንባር ተገጭቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። የእንግዳው ቡድን የአቻነት ጎል ፍለጋ ላይ ያተኮረ ማጥቃት ከኋላ የሚፈጥረው ክፍተት ለአዳማዎች ምቹ ሆኖ ፈጣኖቹ የቡድኑ አጥቂዎች በሽርግግሮች ወቅት በቶሎ ወደ ግብ እንዲደርሱ ሁኔታዎችን አመቻችቶላቸዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይም አዲስ ህንፃ ከመሀል ወደ ሳጥን የጣለውን ኳስ የወልዋሎ ተከላካዮች መዘናጋት ታክሎበት ቡልቻ ሹራ በተረጋጋ ሁኔታ አብርዶ ወደ ግብ ለውጦታል። 

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ከነዓን ማርክነህን በብሩክ ቃልቦሬ ለውጠው ያስወጡት አዳማዎች ወልዋሎዎች ይበልጥ ክፍተት እንዳያገኙ ማድረግ ሲችሉ የመስመር ጥቃታቸውን ለመጨመር ራምኬል ሎክን በስምኦን ማሩ የተኩት ወልዋሎዎች ግን እንዳሰቡት ጫና ሲፈጥሩ አልታየም።

የጨዋታው የመጨረሻ 25 ደቂቃዎች በንፅፅር ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የተሰዋለባቸው ነበሩ። እንደቀደሙት ደቂቃዎች የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ በሚገኝ ክፍተት ፈጣን ኳሶችን ወደ ፊት ከመጣል ይልቅ ኳሱን መያዝ ላይ ያተኮሩት አዳማዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ የግል ብቃቱን ተጠቅሞ በቀኝ መስመር ተከላካዮችን አልፎ ከሞከረው ኳስ በኋላ ጨዋታው ደቂቃዎች ሲቃሩት በረከት ሳጥን ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች ያገኛቸው ያልተጠቀመባቸውን ሙከራዎች ብቻ ነበር ማድረግ የቻሉት። ያም ቢሆን የሁለት ግብ ልዩነቱን ማስጠበቅ ሳይሳናቸው ጨዋታውን አጠናቀዋል። እንግዶቹ ወልዋሎዎች የባለሜዳዎቹን ፈጣን ተጫዎቾች ያገኙት የንበረውን ክፍተት መቀነስ ቢቹሉም ያልተደራጀው የመልሶ ማጥቃት አካሄዳቸው የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳይፈጥርላቸው ጨዋታውን ለማጠናቀቅ ተገደዋል።

በጨዋታው ሦስት ነጥቦችን ያሳካው አዳማ ከተማ ሁለት ደረጃዎችን አሻሽሎ 9ኛ ላይ ሲቀመጥ ወልዋሎ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት ተገዷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ