ሪፖርት| አመዛኝ ክፍለ ጊዜውን በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር የተጫወተው ጅማ አባ ጅፋር ድሬዳዋን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ላይ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር 2-1 አሸንፏል። ያለ ዋና አሰልጣኙ ወደ ሜዳ የገባው ጅማ ከ80 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ የተጫዋቾች ቁጥር ለመጫወት ቢገደድም አሸንፎ መውጣት ችሏል።

በጅማ በኩል ባለፈው ሳምንት በሀዋሳ ከተሸነፈው ስብስብ በሰዒድ ሀብታሙ፣ አብርሀም ታምራት እና ብሩክ ገብረዓብ ምትክ መሐመድ ሙንታሪ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ እና ተመስገን ደረሰ ወደ ሜዳ ሲገቡ ዋና አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በወላጅ አባታቸው ህልፈት ምክንያት ጨዋታውን መምራት ሳይችሉ ቀርተዋል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ከስሑል ሽረ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ አማረ በቀለን በያሬድ ዘውድነህ፣ ዋለልኝ ገብሬን በያሬድ ታደሰ ምትክ ተጠቅሟል።

አዝናኝ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በፈጣን እቅስቃሴ በመጀመያዎቹ አምስት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል። ገና በ4ኛው ደቂቃም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር ኤርሚያስ ኃይሉ ኳስን እየገፋ ገብቶ ወደ መሐል ሲያሻግር ኳሷን ለማዳን በሚደረግ ርብርብ ውስጥ ብዙዓየሁ እንደሻው ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት  ኤርሚያስ ኃይሉ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ጅማዎች በጊዜ ባገኙት ጎል አጀማመራቸውን ቢያሳምሩም በ7ኛው ደቂቃ ተከላካያቸውን በቀይ ካርድ አጥተዋል። መሐመድ ሙንታሪ ኳስ በሚያቀብልበት ወቅት አዳልጦት ወድቆ ኳሱ በአግባቡ ለተካላካዮች ባለመድረሱ ከመሐል ሪችሞንድ አዶንጎ አምልጦ ሲወጣ የጅማው ተከላካይ አሌክስ አመዙ ጥፋት በመስራቱ የዕለቱ አርቢትር በላይ ታደሰ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል። ጥፋቱን ተከትሎ የተሰጠውን ቅጣት ምትም በ10ኛው ደቂቃ በረከት ሳሙኤል ከመረብ በማሳረፍ ድሬዳዎችን አቻ ማድረግ ቻለ፡፡
ጅማዎች ገና በመጀመሪዎቹ ደቂቃዎች ከተከላካይ ክፍሉ በቀይ በመውጣቱ እንዲሁም ላስቆጠሩት ግብ ድሬዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው ነገሮችን አክብዶባቸው ነበር።

በዕለቱ የተከላካይ ክፍሉን ወደ መሐል አስጠግተው እየተጫወቱ የነበሩት ጅማዎች ከመሐል እየሾለኩ በሚወጡት የድሬ አጥቂዎች በተደጋጋሚ ሲፈተኑም ነበር። በ13ኛው ደቂቃ ሙኅዲን ሙሳ ከመሐል ሾልኮ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመው አጋጣሚ እንዲሁም ከቀኝ መስመር ቢኒያም ያሻገራቸው አጋጣሚዎች ኦዲንጎ እና ኤልያስ ማሞ ሞክረው ግብ ጠባቂው ያዳነው ኳስ ድሬዎች በጨዋታው ወደ መሪነት ሊሸጋገሩባቸው የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። 

ከ20ኛው ደቂቃ በኃላ ጅማዎች ንጋቱ ገ/ሥላሴን ከመሐል አፈግፍጎ የተከላካይ ክፍሉ እንዲረዳ ከተደረገ በኃላ በአንፃራዊነት ሲረበሽ የነበረውን የኋላ ክፍል ለማረጋጋት ችለዋል። ወደፊት በመሄድ እድሎችን ለመፍጠርም ከኃላ በሚነሱና ወደ ቀኝ መስመር በኤርሚያስ ኃይሉ ያነጣጠሩ ኳሶች እድሎችን የፈጠሩት ጅማዎች በዚሁ አጋጣሚ የተገኘውን እድል ኤርሚያስ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ እየገፍ ገብቶ ያሻገረውን ኳስ ተመስገን ደረሰ አስቆጥሮ በድጋሚ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የተረጋጉት ጅማዎች ተከላካዮችን ከኳስ ጀርባ በማድረግ እና ድሬዎች አደጋ የሚፈጥሩበት የግራ መስመር በመዝጋት የድሬዎችን ጫና መቋቋም ችለዋል። በቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለ ጊዜም ተጠቃሽ ሙከራዎች ሳይስተናገዱ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ያገኙትን እድል ለማስጠበቅ አስበው በሚመስል መልኩ ወደ ሜዳ የገቡት ጅማዎች ኤርሚያስን ኃይሉን አስወጥተው ከድር ኸይረዲንን በማስገባት አብዛኛዎቹን ደቂቃዎች በመከላከል ላይ አመዝነው አልፈው አልፈው በመልሶ ማጥቃት በተመስገን ደረሰ እና ብዙዓየሁ እንደሻው አማካኝነት ወደ ድሬ ግብ ክልል በመድረስ ያለቀላቸው የግብ እድሎችን አምክነዋል። 

ድሬዎች በአንፃሩ እንደነበራቸው የሰው ቁጥር ብልጫ በሁለተኛው አጋማሽ የበላይነቱን ይወስዳል ተብሎ ቢጠበቅም የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወደ ግብ እድልነት መቀየር ተስኗቸዋል። ወደ ኃላ አፈግፍጎ ጥቅጥቅ ብሎ የሚከላከለው የጅማ ተከላካይ ክፍልን ለማለፍ የሚጠቀሙት ተሻጋሪ ኳሶችም ለጅማዎች ምቾት ከመስጠቱ በተጨማሪ በተደጋጋሚ የቁመተ መለሎው የጅማ ግብጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ ሲሳይ ሲሆኑ ተስተውሏል። 

ድሬዎች ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከል በ65ኛው ደቂቃ ኦዶንጎ ሪችሞንድ በቀኝ መስመር ተከላካዮችን አታሎ አልፎ ገብቶ ለኤልያስ ማሞ አመቻችቶለት አማካዩ መትቶ መሐመድ ሙንታሪ ያዳነበት እንዲሁሞ በ86ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ለዳኛቸው የተሻገረለትን ዳኛቸው ከመሐመድ ሙታሪጋር ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ሙከራዎች ተጠቃሽ ነበሩ። ጨዋታውም በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች በሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ ሳይታይበት በባለሜዳው ጅማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ