ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በርካታ ክስተት አስተናግዶ በአቻ ወጤት ተጠናቋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጎንደር ላይ መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ተከታዩ ፋሲል ከነማን ያገናኘው ጨዋታ ሽኩቻዎች፣ ቀይ ካርዶች፣ ውብ ጎል እና ጠንካራ ፉክክር ታይቶበት 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

ፋሲል ከነማ በአስራ ሦስተኛ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታን 2 -0 ካሸነፈው ስብስብ ሀብታሙ ተከስተን በጋብሪል አህመድ እንዲሁም ሰዒድ ሀሰንን በእንየው ካሣሁን በመተካት ነበር ወደ ሜዳ የገባው። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም በተመሳሳይ ከሜዳው ውጪ ወልዋሎን 4-1 ከረታው ስብስብ ያብስራ ተስፈዬ እና ምንተስኖት አዳነን በማሳረፍ  አሜ አህመድ እና ሳላዲን በርጌቾ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥር ረገድ ባለሜዳዎቹ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በረጃጅም ኳሶች ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ ፈረሰኞቹ የተሻሉ ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት የተሻለ ጫና መፍጠር የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በማልሶ ማጥቃት የሚመጡ ረዣዥም ኳሶችን በማረጋጋት እንዲሁም ከርቀት ወደ ግብ በመሞከረ የተሻለ ጥረት ሲያደርግ በነበረው ጌታነህ ከበደ ጫና መፍጠር የቻሉ ሲሆን 4ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከመሐል ወደ ግራ መስመር ለጋዲሳ መብራቴ ያሻገረለትን ኳስ ጋዲሳ ለአቤል አመቻችቶለት አቤል ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂ ያዳነበት የመጀመርያው ሙከራ ነበር።

በጥሩ ተነሳሽነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ዐፄዎቹ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀውን ሙከራቸውን ወደ ግብነት በመቀየር ነበር አጀማመራቸውን ማሳመር የቻሉት። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ከቀኝ መስመር በረጅሙ ወደ ግራ መስመር የገለበጠውን ጥሩ ኳስ በዛብህ መለዮ በደረቱ ለኢዙ አዙካ አመቻችቶለት ናይጄርያዊው አጥቂ ወደ ፊት ገፍቶ በመግባት አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ አርፏል።

በጊዜ መምራት የጀመሩትና የተሻለ የመሐል ሜዳ እንቅስቃሴ የነበራቸው ዐፄዎቹ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ግን ደካማ ነበሩ። በሙከራ ደረጃ 13ኛው ደቂቃ ላይ ኢዙ አዙካ በመስመር ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ሳጥን አሻምቶት በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመልስ የተገኘውን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ወደ ግብ የመታው እና ኢላማውን ያልጠበቀው ሙከራ በመጀመርያ አጋማሽ የሚጠቀስ ብቸኛው አጋጣሚ ነበር።

ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያለመ እንቅስቃሴ ያደረጉት ፈረሰኞቹ በአንፃሩ የጎል ሙከራዎችን በማድረግ የፋሲልን የኋላ መስመር ለመፈተሽ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በ20 እና 24ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ እና ሀይደር ሸረፋ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ አክርረው በመምታት ሙከራ አድርገዋል። በ36ኛው ደቂቃ ላይም አቻ የምታደርጋቸውን ጎል አስቆጥረዋል። ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ መነሻ ካደረገው እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር አሜ አህመድ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ አሻምቶት ሚካኤል ሳማኪ ሲያወጣው ጋዲሳ መብራቴ ደርሶ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

በጎሉ የተነቃቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሁለት ደቂቃ በኋላም ጎል ለማግኘት ጥረት አድርገው አሜ አህመድ ከሳጥን ጠርዝ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው አድኖበት አድኖበታል። የመጀመርያው አጋማሽም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በፋሲል በኩል በሙከራ ደረጃ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ወደ ግብ የደረሱ ቢሆንም ግብ ለማግኘት ሲቸገሩ ተስተውሏል። በእንግዳዎቹ በኩል በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ላይ ቅያሪ ያከናወኑት ፈረሰኞቹ ወደ ኋላ ተስበው መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉ ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴም ታይቶበታል።

ከእረፍት መልስ በሙከራ ረገድ ተሻሽለው የገቡት ዐፄዎቹ በርካታ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ከነዚህ መካከልም 54ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ጠርዝ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሰጠውን ኳስ ሽመክት ጉግሳ ሞክሮ ኢላማውን መጠበቅ ያልቻለው፣ በ58ኛ ደቂቃ ላይ ከግራ ሳጥን  ጠርዝ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ መትቶ ኳስ የግቡን አጋዳሚ ታኮ የወጣበት እንዲሁም 66፣ 69 እና 70ኛ ደቂቃዎች ላይ በሱራፌል ዳኛቸው፣ ኦሲ ማውሊ እና ሙጂብ ቃሲም አማካኝነት የሞከሯቸው ሙከራዎች ወደ ጎል የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

ያገኟቸውን አጋጣሚዎች በመጠቀም ረገድ የተሻሉ የነበሩት እና የሰላ የፊት መስመር ያላቸው ጊዮርጊሶች በጋዲሳ መብራቴ ተጎድቶ መውጣት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መቀዛቀዝ ቢያሳይም 74ኛው ደቂቃ ላይ ከመመራት ወደ መምራት ያሸጋገራቸውን ጎል ማግኘት ችለው ነበር። ከቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ ያሻማውን ኳስ ወደ በፋሲል ከነማ ተከላካይ ተገጭቶ ሲመለስ ከሳጥኑ አቅራቢያ ላይ ቆሞ የነበረው አቤል ያለው ተረጋግቶ ድንቅ ግብ ማስቆጠር ችሏል። የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ ያስቆጠረው አቤል ያለው ደስታውን ባለ መግለፅ ለቀድሞ ክለቡ ያለውን ክብርም አሳይቷል።

ለተቆጠረባቸው ግብ በቶሎ አፀፋ ለመስጠት ወደ እንቅስቃሴ የገቡት ፋሲሎች በ82ኛው ደቂቃ ላይ ባገኙት የፍፁም ቅጣት ምት አማካኝነት ጎል አስቆጥረዋል። ሄኖክ አዱኛ በሱራፌል ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሙጂብ አስቆጥሮ ፋሲልን አቻ አድርጓል። ጊዮርጊሶች በፍፁም ቅጣት ምቱ መሰጠት ላይ ያላቸውን ቅሬታ በዋና ዳኛዋ ሊዲያ ታፈሰ ላይ ሲገልፁም ተስተውሏል።

ከአቻነት ጎሉ በኋላ ቀሪው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በውጥረት የተሞለ ሲሆን 86ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ደሙ እና ሽመክት ጉግሳ በፈጠሩት ግጭት ሁለቱም በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ከክስተቱ በኋላ ፋሲሎች አሸናፊ ለመሆን የሚያስችላቸውን ግብ ለማግኘት ጫና መፍጠር ቢችሉም ከቆሙ ኳሶች እና ከርቀት ከሚሞከሩ ሙከራዎች ውጪ የጊዮርጊስን የተከላካይ ክፍል መስበር አልቻሉም።  ጨዋታውም 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ27 ነጥብ፣ ፋሲል በ26 ነጥብ ተከታትለው አንደኛ እና ሁለተኛ ላይ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ