በሊጉ የዛሬ መርሐ ግብር ትግራይ ስታዲየም ላይ ስሑል ሽረን ግርጌ ላይ ከሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። ሽረዎች ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን ልዩነት የማጥበብ ዕድል ስያባክኑ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የመጀመርያ ነጥባቸው አሳክተዋል።
ስሑል ሽረዎች ባለፈው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ አቻ ከተለያየው ስብስብ ወንድወሰን አሸናፊ (ቀይ) እና አዳም ማሳላቺን በምንተስኖት አሎ እና ክብሮም ብርሀነ ተክተው ገብተዋል። ባለፈው ሳምንት በወላይታ ድቻ ሽንፈት የገጠማቸው ሆሳዕናዎች ደግሞ ከባለፈው ሳምንት ስብስባቸው ደስታ ጊቻሞን በበረከት ወዮሐንስ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
አሰልቺ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ አድራሻ አልባ ረጃጅም ኳሶች በመጣል ላይ ተጠምደው የዋሉበት ነበር።
ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ ብልጫ በወሰዱበት አጋማሽ ባለሜዳዎቹ በረመዳን የሱፍ እና ክፍሎም ገብረህይወት አማካኝነት የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ክፍሎም ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መቶት አቤር ኦቮኖ ያወጣው ኳስ በአጋማሹ ከታዩት ሙከራዎች የተሻለ ለግብ የቀረበ ነበር። በአጋማሹ የሽረዎች ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ የነበረው ዐወት ገብረሚካኤል ከመስመር አሻምቶት አቤር አቮኖ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራም ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል ያልፈጠሩት ሆሳዕናዎች የተሻለ በተንቀሳቀሱባቸው ደቂቃዎች ጥቂት የግብ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አፈወርቅ ኃይሉ ከቅጣት ምት እና ይሁን እንደሻው ከርቀት አክርረው መትተው ምንተስኖት አሎ ያዳናቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም ቢስማርክ ኦፖንግ በሳጥን ውስጥ ተከላካይ አልፎ በመግባት ያደረገው ሙከራም ሌላ ተጠቃሽ ሙከራ ነው።
እንግዶቹ ተሽለው የተንቀሳቀሱበት ሁለተኛው በርካታ አጨቃጫቂ የዳኝነት ውሳኔዎች የታዩበት ነበር። በተለይም በቆሙ ኳሶች በነበሩት እንቅስቃሴዎች እና ከጨዋታ ውጭ በተባሉት ውሳኔዎች ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥያቄ ተነስቶባቸዋል።
ወደ አጥቂዎቹ በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ነብሮቹ ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ንፁህ የግብ ዕድሎች ፈጥረዋል። ከነዚህም ሱራፌል ዳንኤል በመልሶ ማጥቃት ይዞት የሄደውን ኳስ መቶ ተከላካዮች የተደረቡበትን በድጋሜ አግኝቶ በመምታት ያደረጋት ጥሩ ሙከራ እና አዩብ በቀታ ከይሁን እንደሻው ከቅጣት ምት ያሻማትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረጋት እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ይጠቀሳሉ።
ያፈገፈገውን ተጋጣሚ አስከፍተው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የተቸገሩት ባለሜዳዎቹ የተጫዋቾች ቅያሪ ካደረጉ በኃላ የተሻለ ቢንቀሳቀሱም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ሽረዎች ካደረጓቸው ሙከራዎችም ክፍሎም ገብረህይወት ከተከላካዮች ሾልኮ በግንባር ጨርፎ ያደረገው እና መድሀኔ ብርሀኔ አማካዩ ኃይለአብ ኃይለሥላሴ ያሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ የተሻሉ ለግብ የቀረቡ ነበሩ።
አሰልቺ እና በሙከራዎች ያልታጀበው ጨዋታ በአቻ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የመጀመርያ ነጥባቸውን ከሆሳዕና ጋር ሲያሳኩ ሽረዎች የመሪዎቹን ነጥብ መጣል ተጠቅመው ልዩነታቸው የማጥበብ ወርቃማ ዕድላቸውን አባክነዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ