ሪፖርት| ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ያሳካው ወላይታ ድቻ ደረጃውን ማሻሻሉን ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥሎ ሲውሉ ወላይታ ድቻ በሜዳው ባህር ዳር ከተማን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል።

ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት የአስራ ሦስተኛው ሳምንት ጨዋታ ከሜዳቸው ውጪ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረታው የመጀመሪያው አሰላለፍ ውስጥ የአንድ ተጫዋች ለውጥ በማድረግ ባዬ ገዛኸኝን በያሬድ ዳዊት ተክተው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በአንፃሩ በሜዳቸው ሰበታን አሸንፈው የመጡት ባህር ዳር ከተማዎች በሦስት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርገዋል። ፅዮን መርዕድ፣ ፍፁም ዓለሙ እና ዜናው ፈረደን በሀሪስተን ሄሱ፣ ደረጀ መንግሥቱ እና ፍቃዱ ወርቁ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ስታድየም ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በደጋፊ ተሞልቶ ከጨዋታው አንድ ሠዓት ቀደም ብሎ ነበር ስታዲየሙ የሞላው፡፡

ብዙም ሙከራ ያልተደረገበት እና አሰልቺ የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ረዣዥም ኳስ ለይ ያተኮረ አጨዋወት ይዘው ነበር የቀረቡት፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛው ደቂቃ ከእድሪስ ሠዒድ የተሻገረለትን ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት የመታትን ኳስ ግብ ጠባቂው ሀሪስተን ሄሱ በቀላሉ የያዘበት በባለሜዳዎቹ በኩል የመጀመርያ ሙከራ ሲሆን በ12ኛ ደቂቃ ከዳንኤል ኃይሉ ከመሐል ሜዳ ያሻገረለትን ኳስ ስንታየው መንግሥቱ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በቀላሉ የያዘበት በእንግዶቹ በኩል ቀዳሚው ነበር፡፡

በረዣዥም ኳስ እድል ለመፍጠር አልመው መጫወት የቀጠሉት ድቻዎች በአጨዋወቱ እምብዛም የግብ ዕድል መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን ከርቀት እና ከቆሙ ኳሶች ውጪ ግልፅ እድል መፍጠር ተስኗቸው ታይቷል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ከርቀት መትቶ ኳስ ሀሪስተን ሄሱ ያዳነበት እና 36ኛ ደቂቃ ቸርነት ጉግሳ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ አንተነህ ጉግሳ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው የያዘበት እንዲሁም 42ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ ዓለማየሁ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ የባህር ዳር ተከላካዮች በግምባር ገጭተው ሲመልሱት ሳጥኑ አካባቢ የነበረውና ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ ሞክሮት ኳስ በግቡ አናት ላይ የወጣው የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ባህር ዳሮች ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉ ሲሆን ያለ ጎል ወደ እረፍት ያለየመራሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት 45+2ኛው ደቂቃ ላይ የተጎዳው ደጉ ደበበን ተክቶ የገባው ባዬ ገዛኸኝ ከእዮብ ዓለማየሁ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ሁለት ጊዜ ወደፊት በመግፋት በጥሩ ከጨራረስ የጨዋታውን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። የመጀመሪያው አጋማሽም በዚህ መልኩ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች የተሻለ ጨዋታውን ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን ጥሩ ጥሩ የጎል እድሎችንም መፍጠር ችለዋል። 51ኛ ደቂቃ ላይ ከሳሙኤል ተስፋዬ የተሻገረለትን ኳስ ስንታየሁ መንግሥቱ ሁለት የድቻ ተከላካዮችን በማለፍ የሞከረው ኳስ ኢላማዋን ሳይጠብቅ ወደ ውጭ የወጣበት እና ፡70ኛው ደቂቃ ላይ ደረጀ መንግሥቱ ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ዳግማዊ ሙሉጌታ ነፃ ሆኖ በግንባር ገጭቶ በጎሉ አናት ለይ የወጣበት የሚጠቀሱ ነበሩ።

ከእረፍት መልስ እምብዛም ወደ ጎል መድረስ ያልቻሉት ድቻዎች በአንፃሩ በ84ኛ ደቂቃ እድሪስ እና ባዬ ገዛኸኝ ተቀባብለው ወደ ጎል የደረሱትን ኳስ ፀጋዬ ብርሀኑ አግኝቶት የሞከረውና ወደ ውጭ ከወጣበት ውጪ ጥሩ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። የጨዋታው መገባደጃ ለይ ጫናቸውን ጨምረው የተጫወቱት የጣና ሞገዶቹ በ85ኛ ደቂቃ ላይ ዳግማዊ ሙሉጌታ ከመስመር ያሻገራትን ኳስ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ስንታየው መንግሥቱ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ በግሩም ብቃት ታክሎበት ጎል ከመሆን አዳናት እንጂ ቢያንስ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት በእጅጉ ቀርበው ነበር፡፡ ከዚህች ሙከራ በኋላ የባህር ዳር ተጫዋች ተቀይሮ ለመግባት ሠውነት በማሟሟቅ ላይ እያለ ከድቻ ደጋፊዎች ጋር ሠጣ ገባ ውስጥ የገባ ቢሆንም የደጋፊ አስተባባሪዎች ሁኔታውን አረጋግተዋል። ጨዋታውም በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠረ ጎል በድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ድሉን ተከትሎ ከአምስት ጨዋታዎች በፊት በሰንጠረዡ ግርጌ የነበረው ወላይታ ድቻ በግሩም ፍጥነት አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ባህር ዳር ከተማ አሁንም ከሜዳውውጪ ማሸነፍ ሳይችል ቀርቷል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ