በአስራ አራተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ አባጅፋር በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 2-1 ከረታ በኃላ የሁለቱም ክለብ ረዳት አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“ግብ ካገባን በኋላ አጥቂ ቀይረን ለመከላከል ተከላካይ አስገብተናል” የሱፍ ዓሊ (የጅማ አባጅፋር ረዳት አሰልጣኝ)
ስለጨዋታው
በዛሬው ጨዋታ እንዳያችሁት ተጫዋቾቹ በሰሩት ልምምድ መሠረት ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ሆነን በመጫወት ነበር ውጤት ይዘን የወጣነው። ድሬዳዋ እያንሸራሸረ የሚጫወት ቡድን ነው፤ እኛ ደግሞ እነሱን ተጭነን ነበር ኳሱን ስንጫወት የነበረው። በቀይ ተጫዋች ማጣታችን ትንሽ በኛ ላይ ክፍተት የነበረው። ጎል እስክናገባ አጥቂዎችን አልቀየርንም ነበር። ግብ ካገባን በኋላ ግን አጥቂ ቀይረን ለመከላከል ተከላካይ አስገብተናል፡፡
ተከላካዮች ስለመረበሻቸው
አሌክስ (በቀይ የወጣው) ሁለተኛ ጨዋታው ነው፡፡ በድግግሞሽ ሲሰራ ነው ከነ መላኩ ጋር መስተካከል የሚችለው፡፡ ይሄን እያስተካከልን መሄድ ነው፡፡ መጀመሪያ ላይ አጥቅተን ነበረ እየተጫወትን የነበረው። ቀይ ካርድ ተጫዋች ወጥቶብን ማጥቃትም አልተውንም። ጎል ከገባ በኃላ ግን ተከላካይ ነው የቀየርነው፡፡
“ራሳችን ባመከናቸው ኳሶች ዋጋ ከፍለናል” ፍስሀ ጥዑመልሳን (የድሬዳዋ ከተማ ጊዜያዊ አሰልጣኝ)
ስለጨዋታው እና የቁጥር ብልጫውን ያለመጠቀም
በዛሬው ጨዋታ ራሳችን በሳትነው ዋጋ ከፍለናል፤ ያለውን ነገር አስተካክለን ለቀጣይ መቅረብ ነው፡፡ ቁጥር ብልጫው እንኳን ችግር የለውም። አንድ ቡድን ተጫዋች ሲወጣበት በስነልቦናው ይጠነክራል። ዞሮ ዞሮ ሰበብ ሊሆን አይችልም። የአንድ ሰው ቁጥር ብልጫውን መጠቀም ነበረብን። ያም ሆነ ይህ እንደተጀመረ የሳትናቸው ኳሶች ዋጋ አስከፍለውናል። በዳኛውም በምንም በማንም ማሳበብ አልፈልግም፡፡
ከእረፍት በኃላ ኳስ አልተጫወትንም። ሰው ሲተኛ ነው የዋለሁ። የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የትም መድረስ አለመቻሉ ነው፡፡ ሰው እየተኛ በዛው ተጠናቀቀ። አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል፤ ብዙ ስተንም ነበር። በሁለት ተከላካይም ነው የተጫወትነው። አንዳንዴ ነው ሶስት ሲሆኑ የነበርነው። ሌሎቹን ጠቅላላ የነሱ ሜዳ ውስጥ አድርገን ነው የተጫወትነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ