ስሑል ሽረዎች ሀዲያ ሆሳዕናን አስተናግደው ካለ ግብ አቻ ከተለያዩ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።
“በጉዳት ምክንያት ያደረገናቸው አስገዳጅ ቅያሬዎች ጨዋታውን በፈለግነው መንገድ እንዳንቀጥል አድርገውናል” መብራህቶም ፍስሀ (የስሑል ሽረ ምክትል አሰልጣኝ)
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው በቡድናችን በኩል ከባለፉት ሳምንታት የደከመ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ምክንያቱም በተጫዋቾቻችን ጫናዎች አሉ። ጉዳት ያለባቸው፣ ከነጉዳታቸው ወደ ጨዋታ የገቡ እና በቅጣት ያልገቡ ተጫዋቾች አሉ። ሌላው ደግሞ በጉዳት ምክንያት ያደረገናቸው አስገዳጅ ቅያሬዎች ጨዋታውን በፈለግነው መንገድ እንዳንቀጥለው አድርገውናል።
ሀዲያዎች ጥሩ ተከላክለዋል። በዛ ምክንያትም እንደባለፉት ጨዋታዎች ብዙ ዕድሎች መፍጠር አልቻልንም። በአጠቃላይ ድካሞ እና ያሉት አንዳንድ የጠቀስኳቸው ነገሮች ጥሩ እንዳንቀሳቀስ አድርገውናል።
በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ዘግቶ የሚጫወት ቡድን ሲያጋጥመን እንዴት ማስከፈት እንዳለብን እንሰራበታለን። በቀጣይ ሳምንት ከባህር ዳር ጋር የምናደርገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ነው የምንገባው፤ ምክንያቱም ዛሬ ወሳኝ ነጥብ ጥለናል።
“በፈታኝ ሰዓት ነው ቡድኑን የተረከብኩት፤ ፈተናውንም በአግባቡ ለመወጣት ጠንክሬ እሰራለሁ” ፀጋዬ ኪዳነማርያም (ሀዲያ ሆሳዕና)
ስለ ጨዋታው
ሥራውን ከተረከብኩ ገና አንድ ሳምንቴ ነው። ተጫዋቾቹ በውድድር ላይ እያሉ ነው ያገኘኋቸው። ከዛ በተጨማሪም ነባር የአሰልጣኞች ቡድን አባላት የሉም፤ ክለቡም ለቀዋል። በዛ ምክንያት አንዳንድ መረጃዎች የማግኘት ችግሮች አሉ።
በፈታኝ ሰዓት ነው ቡድኑን የተረከብኩት። ፈተናውንም በአግባቡ ለመወጣት ጠንክሬ እሰራለሁ። ከተጫዋቾቼ ፣ ከአመራር እና ከቡድናችን ደጋፊዎች ተባብሮ በድምር ጥሩ ስራ መስራት ነው እቅዳችን። ዋና ዓላማችን ያሉንን ክፍተቶች አርመን በሁለተኛው ዙር ደረጃችንን ማሻሻል ነው። ደረጃችን ትንሽ ወረድ ብሏል። ሆኖም የማይሻሻልበት ምንም ምክንያት የለም።
በሁለተኛው ዙር በቂ የዝግጅት ጊዜም ስላለን የተቻለንን ሁሉ አድርገን ቡድኑን በሊጉ ላይ ማቆየት ነው።
ስለ ቡድኑ አጠቃላይ ሁኔታ
ለቀረችን አንድ ጨዋታ በስነ-ልቦና ነው የምናዘጋጀቸው። ሊጉ ገና ነው። በሁለተኛው ዙር እያንዳንዱ ጨዋታ እንደ ጥሎ ማለፍ በትኩረት ከተጫወትን የሚከብድ አይደለም። ባለፈው ጨዋታ ጥሩ ተንቀሳቅሰን ብዙ የግብ ዕድሎችም ፈጥረን ተሸንፈናል። ለሁለተኛው ዘር ቡድናችን መሻሻሎት ያስፈልጉታል። ስር ነቀል ለውጥ ሳይሆን ትንሽ ጥገና ያስፈልገዋል። እነሱን ክፍተቶች ለመሙላት ሊጉን የሚያቁት ተጫዋቾች ያስፈልጉናል። እንደሚታየው ትንሽ የልምድ እጥረትም አለን። ከላያችን ላይ ያሉት ቡድኖች ብዙም አልራቁም። ሁለተኛው ዙር ሲጀመር አሻሽለን በሊጉ ላይ እንቆያለን።
© ሶከር ኢትዮጵያ