የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

በሊጉ 14ኛ ሳምንት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ ያደረጉትና በድቻ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ከባድ ጨዋታ ነበር” ደለለኝ ደቻሳ (ወላይታ ድቻ)

ጨዋታው በሜዳችን በመሆኑ አጥቅተን ለመጫወት ነበር የገባነው። እንዳያችሁት ከባድ ጨዋታ ነበር፤ ባህር ዳር ጥሩ ቡድን ነው፡፡ በአጠቃላይ ስናየው የዛሬው ጨዋታ ለኛ በጣም አስፈላጊ እንደመሆኑ ደጉን ከነ ጉዳቱ ነበር ያሰለፍነው፡፡

እግርኳስ አንድነትና ህብረት ይፈልጋል። እኛ ቡድን ውስጥ የሚታየው ነገር ፍላጎታችን በጣም ጨምሯል። እዛ ነገር ላይ ክፍተቶቻችን ምንድናቸው የሚለውን በጋራ እየሰራን ስለሆነ ነው ይመስለኛል ውጤታማ የሆንነው፡፡



“ሁለት የተለያዩ 45 ደቂቃዎች ነው ያሳለፍነው” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

በመጀመሪያ ለወላይታ ድቻዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሁለት የተለያዩ 45 ደቂቃዎች ነው ያሳለፍነው። በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ከክንፍ የሚመጡ ተሻጋሪ ኳሶችን ተከላክለን የራሳችንን ጨዋታ ለመጫወት ነበር የሞከርነው ነገር ግን እንደምናስበው አጥቅተናል ወይም የግብ እድል ፈጥረናል ማለት አልችልም። በተለይ ሁለተኛ ኳስ ላይ ደካማ ነበርን፡፡ በሁለተኛው 45 በአብዛኛው ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በደንብ ተጭነን ጎሎችን ለመፍጠር ሞክረናል። ያሰብነውን ያህል የጎል ዕድል ባንፈጥርም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻልን ነበርን። ጎል ማግባት አልቻልንም፤ እነሱም ያገቡትን ጎል አስጠብቀው መውጣት ችለዋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ