በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐግብር አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ 11 የማስጠንቀቂያ ካርዶች በታዩበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከሰበታ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።
ሰበታ ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ ከተሸነፈው ስብስብ ውስጥ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ በደሳለኝ ደባሽና ባኑ ዲያዋራ ምትክ አቤል ታሪኩና ሲላ ዓሊ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ውስጥ ግብ ጠባቂው በረከት አማረን በተክለማርያም ሻንቆ እና አጥቂው እንዳለ ደባልቄን በአቡበከር ናስር ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የሰበታ ከተማዎች በተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በቁጥር በረከት ቢሉም ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩበት መንገድ እጅግ ያልተቀናጀና ለኢትዮጵያ ቡናዎች በቀላሉ የመመስረቻ አማራጮችን የፈጠረ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻለ እንዲንቀሳቀሱ እድል የፈጠረ ነበር። በሰበታዎች በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው ኢብራሂም ከድር የጊዜ አጠባበቅ እንዲሁም በወሳኝ የጨዋታ ቅፅበቶች ያለው ደካማ የቦታ አያያዝ በተለይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ለፈጠሯቸው አጋጣሚዎች ዋነኛ መነሻ እንዲሆን ያስቻለ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደፈጠሯቸው አጋጣሚዎች ግብ ማግኘት ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በ5ኛው ደቂቃ አቤል ከበደ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን አጋጣሚ ለአቡበከር ያቀበለውና አቡበከር በተከላካዮች መካከል ያሳለፈለትን ኳስ ሚኪያስ ተቆጣጥሮ በመምታት ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ሙከራ ወደ ግብ መድረስ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በ16ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከቅጣት ምት ሞክሯት ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት እንዲሁም በ19ኛው ደቂቃ ላይ አከታትለው አሥራት ቱንጆ ከመስመር አጥብቦ ገብቶ ወደ ግብ የላከው እንዲሁም በተመሳሳይ ሂደት ዳንኤል አጃይ ኳስ በማቀበል ወቅት በሰራው ስህተት የተገኘውን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ወደ ግብ የላካቸው ተከታታይ ኳሶች ሁለቱም በግቡ ቋሚ የተመለሱባቸው አጋጣሚዎች እጅግ አስቆጭ ነበሩ።
ሰበታዎች ደካማ በነበሩበት የመጀመሪያ አጋማሽ አዲስ ተስፋዬ በቀጥታ ከቅጣት ምትና ፍፁም ወደ ግብ ሲሞክራት የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ተረባርው ካዳኑባቸው ኳስ ውጭ ተጠቃሽ የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚሁ አጋማሽ በተለይ ሲይላ ዓሊ እና አቤል ታሪኩ በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ውጭ እንደቡድን የሚጠቀስ መልካም ጎን ለመፈለግ እጅግ ከባድ የነበረ አጋማሽ አሳልፈዋል።
በርከት ያሉ የማስጠንቀቂያ ካርዶች በተመዘዘዙበት በዚሁ አጋማሽ ቡናዎች ተጨማሪ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ21ኛው ደቂቃ ዳንኤል አጃይ ቦታውን መልቀቁን ተመልክቶ ታፈሰ ሰለሞን ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ የላከውን ኳስ ዳንኤል እንደምንም ተመልሶ በግሩም ብቃት ያዳነበት እንዲሁም በ24ኛው ደቂቃ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ታፈሰ ሰለሞን ከሰበታ ተከላካዮች ጀርባ በነበረው ሰፊ ክፍት ቦታ ላይ የደረሰውን ኳስ ማስቆጠር ሲችል ለአቡበከር አቀብሎት ኳሱ ቢቆጥርም ከጨዋታ ውጭ ተብሎ ሊሻርባቸው ችሏል።
ምንም እንኳን በአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ሰበታዎች ወደ ጨዋታው የመመለስ ምልክት ቢያሳዩም የቡናዎች የበላይነት የታየበት አጋማሹ ከመደምደሙ በፊት በ43ኛው ደቂቃ አቡበከር ከተከላካዮች ጀርባ ያሾለከለትን ኳስ አቤል ደርሶ አስቆጠረ ሲባል ዳንኤል ደርሶ ባዳነበት ሙከራ ነበር ሁለቱ ቡድኖች ያለ ግብ ለእረፍት ወደ መልበሻ ቤት ያመሩት።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ ሁለቱም ቡድኖች በኩል የግብ ሙከራዎች በተመለከትንበት ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የሚባልን እንቅስቃሴን ማሳየት ችለዋል።
በ48ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ወደ ግራ ከጠበበ ቦታ ላይ ከቅጣት ምት አሻማ ተብሎ ሲጠበቅ ታደለ መንገሻ በቀጥታ ወደ ግብ በላካትና ተክለማርያም ሻንቆና የግቡ ቋሚ ተጋግዘው በመለሱበት ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ሰበታዎች ከመጀመሪያው በተሻለ እንደ ቡድን በቁጥር በዝተው ለመከላከልና ፈጠን ባሉ መልሶ ማጥቃቶች አደጋ ለመፍጠር ሲሞከሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደመጀመሪያው ሁሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ማጥቃትን መሰንዘር አድርገው ቢጫወቱም ውጤቱን በእጅጉ ከመፈለጋቸው የተነሳ ጥድፊያዎች የተስተዋሉበትን እንቅስቃሴን አስመልክቶናል።
ሰበታዎች በ52ኛው ደቂቃ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ ፍፁም ገ/ማርያም ፈቱዲን አልፎ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ ወደ ውጭ በወጣበት እንዲሁም በ56ኛው ደቂቃ በተከታታይ ታደለ መንገሻ ከቅጣት ምት እና ሲይላ ዓሊ በሁለት አጋጣሚዎች ከማእዘን ምት እና ከመስመር ከተሻገረ ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ያመከናቸው ኳሶች ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
የማሸነፊያ ግብ ለማግኘት ጥድፊያ ውስጥ የገቡ የሚመስሉት ቡናዎች ሙከራ ማድረጋቸውን ቀጥለው በ53ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ በተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ኳስ አቡበከር ከዳንኤል ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አመከናት እንጂ አስቆጭ ሙከራ ነበረች። እንዲሁም በ79ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ከጉዳት ጋር እየታገለ ጨዋታውን ያከናወነው አቡበከር ናስር በሁለት አጋጣሚ ወደ ግብ ቢሞክርም የሰበታ ተጫዋቾች ተረባርው ሊያድኑበት ችለዋል።
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ሰበታዎች ሁለት ድንቅ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመስዑድ እና ባኑ ዲያዋራ አማካኝነት ሲያመክኑ ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በወንድሜነህ ደረጀ አማካኝነት እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ አምክነዋል። ጨዋታውም ጎል ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።
በጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ከጉዳቱ በበቂ መልኩ ያገገመ የማይመስለው የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ አቡበከር ናስር እያነከሰ ጨዋታውን ያጠናቀቀበት ቁርጠኝነት አድናቆት የሚቸረው ሆኖ አልፏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ