የአሰልጣኞች አስተያየት | ሰበታ ከተማ 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

በ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ጋር 0-0 ከተለያዮበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
” በሁለታችንም በኩል ክፍት ጨዋታ ነበር፤ ተመልካች ጥሩ እንቅስቃሴ ተመልክቷል ብዬ አስባለሁ” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለጨዋታው

” በሁለታችንም በኩል ክፍት ጨዋታ ነበር፤ ተመልካች ጥሩ እንቅስቃሴ ተመልክቷል ብዬ አስባለሁ። ተጫዋቾቼ የምንፈልገውን ነገር በድፍረት እንዳያደርጉ አንዳንድ ግልፅ ያልሆኑ ስህተት የነበሩባቸው የዳኝነት ውሳኔዎች ያስገደዳቸው ይመስለኛል። ዳኛው ጨዋታውን ለመቆጣጠር በማሰብ በርካታ ካርዶችን መምዘዙ የጨዋታው እንቅስቃሴ እንዲቆረጥ አድርጎታል። እንደአጠቃላይ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ጨዋታ ነበር።”

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የነበረውን የማጥቃት ተነሳሽነት ስላለማስቀጠላቸው

” የእግርኳስ ጨዋታ 90 ደቂቃ ነው፤ መሉ 90 ደቂቃውን ብቻህን አይደለም የምትጫወተው። ተጋጣሚ አለ፣ የሚኖሩ ጫናዎች አሉ፣ የምትፈልገው ውጤት አለ። ስለዚህ ከዚህ አንፃር እንዲሁም የእነሱ በተደጋጋሚ ወደ እኛ ግብ መድረሳቸው አንፃር በተመሰነ መልኩ የእኛ ልጆች ወደ ኃላ ሸሽተው ነበር። 90 ደቂቃ ክፍት የነበረ ጨዋታ ነበር አሸንፈን ብንወጣ የተሻለ ነበር። ነገር ግን አቻ መውጣታችን የሚያስከፋ አይደለም።”

“በሁለተኛው አጋማሽ ጎል ያስፈልገን ስለነበር ትንሽ ጥድፊያ የበዛበት ነበር” ካሳዬ አራጌ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

” ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ጎል ያስፈልገን ስለነበር ትንሽ ጥድፊያ የበዛበት ነበር።”

ረጃጅም ኳሶች በሁለተኛው አጋማሽ ስለመብዛታቸው

” ተጋጣሚዎቻችን ይዘው ከሚመጡት ነገር አንፃር እኛ የምናስባቸው ነገሮች አሉ። እስካሁን ድረስ አብዛኛዎቹ የገጠምናቸው ቡድኖች በሶስት የተለያዩ መንገዶች ይቀርባሉ። ነገርግን ባለፈው ሳምንት ወልቂጤዎች በተለየ መንገድ (አራተኛው መንገድ) ቀርበዋል። ስለዚህ እነዚህን በመንተራስ እኛ ሁለተኛ አማራጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ተጋጣሚያችን ሁኔታ እስከ አራተኛ አማራጭ ድረስ ይኖሩናል ማለት ነው። ረጃጅም ኳሶች ከዚህ በፊት የሚደረጉ ነገሮች ናቸው። ምናልባት ዛሬ አንዳንዶቹ ረጃጅም ኳሶች ውጤታማ ስለነበሩ በዛ መልኩ ለመጠቀም ያሰብን ይመስል የነበረው እንጂ ከዚህ ቀደምም ይደረጉ ነበር። ነገርግን የቅብብል ስህተቶች ስለነበሩባቸው ዛሬ የተለየ መሰለ እንጂ በፊትም የነበረ ነው።”

ስለዳኝነት

“ዳኞችን በተመለከተ ሁለት አይነት ነገር ነው ያለኝ፤ አንደኛው ከዚህ በፊት ተናግሬዋለሁ። ዳኞች በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች እየታገዙ ያሉት ከዳኞች የተሰወረ ነገር ስላለ ነው። ስለዚህ ያሉትን ስህተቶች በዛ መልኩ ተረድቶ መታገስ ያስፈልጋል። ሁለተኛው ሁሌም የምለው ነገር ዳኞቻችን ከስሌት ውስጥ መውጣት አለባቸው። ይሄ ቡድን እየተመራ ነው እዚህ ጋር ቅጣት ሰጥቼባቸዋለሁ ምናምን ከሚሉ አስተሳሰቦች መውጣት አለባቸው። ከዛ ውጭ ያሉ ከህግ አንፃር ያሉ ስህተቶችን ግን መታገስ ያስፈልጋል። ”

© ሶከር ኢትዮጵያ