ዛሬ በብቸኝነት የተካሄደው የከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ ጨዋታ በደደቢት እና ወሎ ኮምቦልቻ መካከል ተከናውኖ ያለ ጎል አቻ ተለያይተዋል።
ይጀመራል ከተባለበት ሰዓት ሀያ ደቂቃ ዘግይቶ የጀመረው ይህ ጨዋታ በሜዳው ለበዓል ማክበርያ ተብሎ የተቀመጠው መድረክ እስኪወጣ ድረስ ነው ጨዋታው ዘግይቶ የጀመረው።
ማራኪ ባልነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች እየተፈራረቁ የበላይነት የወሰዱበት ሲሆን በእንቅስቃሴ ረገድ ግን በሁለቱም በኩል አሰልቺ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። በጨዋታው በረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ደደቢቶች ከሳጥን ውጭ በተሞከሩ በርካታ ኳሶች ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አፍቅሮት ሰለሞን እና ሙልጌታ ዓምዶም ከቅጣት ምት ያደረጓቸው የሙከራዎች የተሻለ ለግብ የግብ የቀረቡ ነበሩ። ደደቢቶች ከተጠቀሱት ሙከራዎች በተጨማሪም ሙልጌታ ዓምዶም ከመስመር አሻምቶት መድሀኔ ታደሰ በግምባሩ ገጭቶ አቡበከር ኑሩ በምያስደንቅ ብቃት ባወጣው ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር።
ወደ ብቸኛ አጥቂው በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ወሎ ኮምቦልቻዎችም በግሩም ሀጎስ እና ዘርአይ ገብረሥላሴ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ግሩም አክርሮ መቶት ሙሴ ዮሐንስ እንደምንም ያወጣው ኳስ ወሎ ኮምቦልቻዎች ከሞከርዋቸው ሙከራዎች የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበር።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ ብዙም ሳቢ ያልነበረው ሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት ነበር። በአጋማሹ ወደ ተጋጣሚ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት እንግዶቹ በመጀመርያው ደቂቃ ብርሀኑ ኦርዴሎ አማካኝነት መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ሆኖም ተጫዋቹ እዮብ ገብረማርያም ያሻገረለትን ኳስ መቶ ወጥቶበታል። ወሎዎች ከሙከራው በኃላም በአሰጋኸኝ ጴጥሮስ እና ሄኖክ ጥላሁን ሙከራዎች አድርገው ብሙሴ ዮሐንስ ጥረት ግብ ከመሆን ተርፈዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የታዩት ሰማያዊዋቹ በአጋማሹ አጀማመር ደካማ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም የተጫዋቾች ቅያሪ ካደረጉ በኃላ በተሻለ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም መድሀኔ ታደሰ ከርቀት አክርሮ ያደረጋት ሙከራ እና ቢንያም ደበሳይ ከመአዝን የተሻገረችን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ጥሩ ሙከራ ይጠቀሳሉ።
ውጤቱ በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ኮምቦልቻ ከመሪው ለገጣፎ የነበረውን ልዩነት የሚያጠብበትን እድል አምክኗል።
© ሶከር ኢትዮጵያ