የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ሲዳማ ቡና

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጪ ወልቂጤን 1-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞቹ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተውናል።

“በምናገኘው ኳስ ነበር ወደፊት ስንሄድ የነበረው፤ ያንን በማድጋችን ተሳክቶልናል” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለጨዋታው እና ስለተፈጠረው ክስተት

ጨዋታው ጥሩ ነበር። እኛ ያው ጎላችንን ጠብቀን ባገኘነው አጋጣሚ ነበር ወደ ፊት ስንሄድ የነበረው። የመረጥነው ጨዋታ መልሶ ማጥቃት ነበር። ይህንንም በማድረግ በተለይ ተከላካይ ቦታ ላይ በዛ አድርገን ተከላካዮቻችን ቆመው እንዲጫወቱ በማድረግ እነሱ የሚጥሉትን ረጃጅም ኳሶች ልጆቹን በአግባቡ ማርክ አድርገናቸው ተቆጣጥረናቸው ስለነበር አልተቸገርንም። በምናገኘው ኳስ ነበር ወደፊት ስንሄድ የነበረው፤ ያንን በማድጋችን ተሳክቶልናል፡፡ ልጆቹ ደግሞ ታክቲካሊ ዲሲፕሊን ስለነበሩ ለዛ ነው ውጤታማ የሆነው፡፡

ከመጀመሩ በፊት ለኛ ደጋፊዎች ቦታ አልተሰጠም ነበር። ያ ደግሞ እያደገ መጥቶ ጨዋታው ሲያልቅ ብዙ ደጋፊዎች ተፈንክተዋል። በዚህ የተነሳ ጨዋታው ካለቀ በኋላ እስከ አስራ ሁለት ሰአት ከሀያ ድረስ ከሜዳ ሳንወጣ ቆይተን በኋላ በፖሊስ ታጅበን ወጥተናል፡፡

“ጨዋታውን ባሰብነው መንገድ መከወን አልቻልንም” ደግአረገ ይግዛው (ወልቂጤ ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታውን ባሰብነው መንገድ መከወን አልቻልንም። በተለይ የመጀመሪያው 45 ልጆቻችን ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው። እንዲሁም የሌሎችን ውጤት አይቶ በመግባታቸው ትንሽ ጫና ውስጥ ነበርን። ጫናው የማሻነፍ ፍላጎት ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ያሰብነውን ያህል አልተቀሳቀስንም ነበር። ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ግን ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ ነበር ልጆቻችን የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከመልካም እንቅስቃሴ ጋር ነበር። ያገኘናቸውን የግብ እድሎች አለመጠቀማችን በዛሬው ጨዋታ ዋጋ አስከፍሎናል። እነሱ አንድ ድል ፈጥረው በሚገባ ተጠቅመው አሸንፈዋል። እኛ ደግሞ ነጥብ አጥተናል።

© ሶከር ኢትዮጵያ