ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከሜዳው ውጪ ወልቂጤን በመርታት ደረጃውን አሻሻለ

በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሜዳው ውጪ ወልቂጤ ከተማን የገጠመው ሲዳማ ቡና 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ያሻሻለበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

ወልቂጤ ከተማዎች ባሳለፍነው ሀሙስ ከቡና ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ በአዳነ ግርማን በበረከት ጥጋቡ ብቻ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ሲዳማዎች በአንፃሩ ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማን ካሸነፈው ቡድናቸው ዳዊት ተፈራ እና ትርታዬ ደመቀን አሳርፈው ግሩም አሰፋ እና አዲስ ግደይን ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ፌደራል ዳኛ ዮናስ ካሳሁን በመራው በዚህ ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ያልታየበት እንዲሁም ኃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ በዝተውበት ነበር። በአንፃራዊነት እንግዳው ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ ተሽለው የተገኙት እንግዶቹ ጎል ያስቆጠሩት ገና በ9ኛው ደቂቃ ነበር። ከወልቂጤዎች በኩል የመጣውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቋረጥ የሲዳማ ተከላካይ በረዥሙ የጣለውን ኳስ ይገዙ ቦጋለ የወልቂጤ ተከላካዮች መዘንጋት ተጨምሮበት በፍጥነት በመውጣት ተረጋግቶ ኳሱን እየገፋ ሳጥን ውስጥ በመግባት ጎል አስቆጥሯል።

ክትፎዎቹ ከመጡበት ተከታታይ ጥሩ ጉዞ አኳያ ብዙም መልካም እንቅስቃሴ ማድረግ ባይችሉም በ23ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተጣለለትን አህመድ ሁሴን በሁለት ተከላካዮች መሐል አልፎ ኳሱ ቢደርስም ግብጠባቂ ከግብ ክልሉ በመውጣት ኳሱን አድኖበታል። ክትፎቹ ወደ ጨዋታው ግብ በማግባት በፍጥነት ለመመለስ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ስኬታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቀራኒው ሲዳማ ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው በፈጣኑ የመስመር አጥቂ አዲስ ግደይ አማካኝነት ጥሩ የጎል አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

የአየር ላይ ኳስ በዝቶበት በዋለው ጨዋታ በ34ኛው ደቂቃም ሀብታሙ ገዛኸኝ ከግራ መስመር ያሻገረውን አዲስ ግደይ በጥሩ ሁኔታ ኳሱን አየር ላይ እያለ መሬት ለመሬት ቢመታውም ለጥቂት የግቡ ቋሚን ተኮ ወጥቶበት ጨዋታው በሲዳማ 1-0 በሆነ መሪነት እረፍት ወጥተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የሲዳማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት የመረጡት አጨዋወት ሰምሮላቸዋል። በአንፃሩ ወልቂጤዎች ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት በዚህ አጋማሽ ሙከራዎች ቢያደርጉም ጎል ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በ50ኛው ደቂቃ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅሙ ወደ ጎል የተመታውን አህመድ ሁሴን ሳይታሰብ ከተከላካዮች መሐል ነፃ ኳስ አግኝቶ በግንባሩ ቢመታውም ወደ ውጭ ሊወጣበት ቻለ እጂ ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በመሐል ሜዳ አብዱልከሪም ወርቁ እና ሳዲቅ ሲቾ አንድ ሁለት ቅብብል አልፈው አብዱልከሪም በመጨረሻም ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ጎል ከመሆን ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ወልቂጤዋች ጫና ፈጥረው በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ሲዳማ ቡና በመልሶ ማጥቃት ከግብ ክልላቸው ለማራቅ ተከላካዮች የመቱትን ኳስ የመጀመርያው ጎል በተቆጠረበት መንገድ ነፃ ኳስ አዲስ ግደይ አግኝቶ ይድነቃቸው ቀድሞ በመውጣት ተጨማሪ ግብ ከመሆን አድኖታል። ይህም በሁለተኛው አጋማሽ በሲዳማ በኩል የተገኘ አደገኛ አጋጣሚ ነበር።

በመልሶ ማጥቃት የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት እየፈተናቸው ባሉበት አጋጣሚ ወልቂጤዎች አቻ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ በ70ኛው ደቂቃ አግኝተው ነበር። ጫላ ከቀኝ ወደ መሐል ኳሱን አጥብቦ ያሻገረውን ኳስ የግብ ክልሉን በዛሬው ዕለት በንቃት ሲጠብቅ የዋለው የሲዳማ ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ቀድሞ በመውጣት አድኖበታል። ብዙም ሳይቆይ አህመድ ሁሴን አምስት ከሃምሳ ውስጥ በግባሩ ሞክሩ በግቡ አናት ወጥታበታለች ለወልቂጤዎች የምታስቆጭ የጎል አጋጣሚ ሆና አልፋለች። የጨዋታው እንቅስቃሴ ቀጥሎ በሌላ አጋጣሚ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ሙሃጅር ያሻገረውን ኳስ ሳዲቅ ሴቾ ለተከላካዮች ጀርባውን ሰጥቶ ወደ ግብ ቢመታውም ፍቅሩ በቀላሉ ይዞበታል።

በጥሩ የመከላከል አደረጃጀት እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት እየተከተሉ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት በከፍተኛ ፍላጎት ብርቱ ትግል ያደረጉት ሲዳማዎች ሰምሮላቸው ጨዋታውን በ1-0 አሸናፊነት አጠናቀዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ወልቂጤ ባለፈው ሐሙስ ከቡና ባደረጉት ጨዋታ ትኬት ቆርጠው ጨዋታውን ሳይመለከቱ የቀሩ ደጋፊዎች ቅሬታቸውን በለክቡ አመራር ላይ ያነሱ ሲሆን ገንዘባቸው ተመላሽ እንዲሆን ጠይቀዋል። ቀስ በቀስ ተቃውሞው ወደ ሁከት ተቀይሮ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ግብግብ የተፈጠረ ቢሆንም በቦታው የነበረው የፀጥታ ኃይል ተቆጣጥሮታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ