ከቅዳሜ እስከ ሰኞ በተደረጉ ጨዋታዎች የተስተዋሉ ትኩረት ሳቢ ተጫዋቾች ነክ ጉዳዮችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።
👉 ባለ ሐት-ትሪኩ ኦኪኪ አፎላቢ
በ2010 የውድድሩ ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ዓመት ቆይታው ከጅማ አባጅፋር ጋር የሊጉ አሸናፊ ሲሆን በ23 ግቦች በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ማጠናቀቅ የቻለው ኦኪኪ ዐምና በግብፅና በኢትዮጵያ ሊጎች የነበረው ቆይታ ብዙም ውጤታማ ናቸው ብሎ ለመናገር አያስደፍሩም።
በክረምቱ ወደ መቐለ 70 እንደርታ ያመራው ኦኪኪ በቋሚነት ተሰልፎ መጫወት ከጀመረበት ከሁለተኛ ሳምንት በኋላ እስከ ዘጠነኛ ሳምንት የጨዋታ ሳምንት ግቦችን ማስቆጠር ባለመቻሉ ተቃውሞዎችን ሲያስተናግድ ቢቆይም 9ኛ ሳምንት ሰበታ ላይ ሁለት ወሳኝ ግቦችን በማስቆጠር ወደ አግቢነት ቢመለስም በስሑል ሽረው ጨዋታ አንድ ግብ አስቆጥሮ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ መወገዱ መልሶ ወደነበረት ጫና እንዲገባ ያስገደደው ይመስላል።
በዚህኛው የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ ላይ ደግሞ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን 5-1 ሲረታ በጨዋታው ድንቅ የነበረው ናይጄሪያዊው አጥቂ በአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያውን ሐት ትሪክ መስራት ችሏል። አማኑኤል ገ/ሚካኤል ላይ የተንጠለጠለውን የግብ ማግባት ኃላፊነት ይጋራል ተብሎ ታምኖበት ወደ ክለብ የተቀላቀለው አጥቂው በሁለተኛው ዙር ይበልጥ በተሻለ ቡድኑን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ከነጉዳቱ የተጫወተው አቡበከር ናስር እና የተክለማርያም ሻንቆ አስገራሚ በራስ-መተማመን
ከሰሞኑ ግብ ለማስቆጠር የተቸገሩት የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በዚህኛው ሳምንት ጨዋታ አቡበከር ናስር ካጋጠመው ጉዳት ሙሉ ለመሉ ሳያገግም ከሰበታ ከተማ ጋር 0-0 በተለያየው የመጀመሪያ ስብስብ ውስጥ አካተውት ሙሉ 90 ደቂቃውን በከፍተኛ ፍላጎት ሲያገለግል ተስተውሏል። ገና ከጨዋታው የማስጀመሪያ ፊሽካ መበሰር አንስቶ ሲያነክስና በተለይ የማፈትለክ ሩጫዎችን ለማድረግ ሲሞክር የህመም ስሜት ይታይበት የነበረው አቡበከር 90 ደቂቃውን ሙሉ በተሻለ ብቃት መንቀሳቀስ ችሏል።
አቡበከር ከእድሜው ለጋነት እና ካለው ከፍተኛ የመጫወት ጉጉት አንፃር ከነህመሙ ለመጫወት ቢሞክርም የቡድኑ የህክምና ቡድን አባላትና አሰልጣኞች ተጫዋቹን በቀጣይ በአግባቡ ከጉዳት ነፃ ሆነ ለመጠቀም በቂ እረፍት በመስጠት ከጉዳቱ እስኪያገግም መጠበቁ የተሻለ ጥቅም የመሆኑ ነገር አያጠያይቅም። ምንም እንኳን ቡድኑ ውጤት መያዝ የግድ የሚለው ወቅት ላይ የሚገኝበት ጊዜ ቢሆኑም በተጫዋቹ ላይ አላስፈላጊ ኃላፊነት (risk) ከመውሰድ ይልቅ በቦታው ባሉ የተጫዋቾች አማራጭ መጠቀም የተሻለ ነው።
ሌላኛው በትናንቱ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና በኩል በግብጠባቂነት የተሰለፈው ተክለማርያም ሻንቆ በጨዋታው ያሳይ የነበረው የራስ መተማመን ደረጃ የሚደነቅ ነበር። ተጫዋቹ በድፍረት ኳሶችን በመቀበልና በማቀበል ለመሐል ተከላካዮቹ እና የተከላካይ አማካዮቹን በቅርበት በመገኘት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች እንኳን ኳስን ለመቀበል የሚያደርገው ጥረት እንዲሁም በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ኳሶችን ይዞ ከሁለቱ የመሐል ተከላካዮች በተወሰነ መልኩ አልፎ ኳሶችን እየገፋ በመግባት ለማቀበል የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው። አሁንም ቢሆን ተንጠላጣይ ኳሶችን የማቀበል አቅሙ (passing range) ላይ የተወሰኑ መስተካከል የሚባቸው ነገሮች ቢኖሩም ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል።
በደካማው የሀገራችን እግርኳስ ነባራዊ ሁኔታ በረኞች በሁለቱ ቋሚዎች መካከል ከመቆም በዘለለ ሚና እንደሌላቸው በሚታሰብበት ደካማ የእግርኳስ አስተሳሰብ ውስጥ መሰል ይህን አስተሳሰብ ሰብረው ግብጠባቂዎች ተጨማሪም ሚና እንደሚኖራቸው እያስተዋወቁ የሚገኙ በሊጉ በጣት የሚቆጠሩ ግብጠባቂዎችን ማበረታት ያስፈልጋል።
👉 አዲሱ የጌታነህ ከበደ ሚና፣ የጋዲሳ ጉዳት እና የሳልሀዲን መመለስ
ከሰሞነኛ የቅዱስ ጊዮርጊስ መሻሻል ውስጥ ሚና እየተወጣ የሚገኘው ጌታነህ ከበደ አሁንም ሜዳ ላይ በሚያሳየው ብቃት ማስደመሙን ቀጥሏል። ካለፉት ዓመታት በተለየ ታታሪ የሆነውን ጌታነህ እያስመለከተን ሲገኝ ወደ ቀድሞው የግብ አነፍናፊነት ደመነፍሱ እየተመለሰ ስለመሆኑ ምልክቶችን እየሰጠ ይገኛል።
ጌታነህ በዚህ ሳምንትም በፋሲሉ ጨዋታ ላይ ከተለመደው የፊት አጥቂነት ሚናው በተለየ በተሰጠው ከአጥቂዎች ጀርባ የአጥቂ አማካይነት አይነተኛሚና ተስፋ ሰጪን እንቅስቃሴ አስመልክቶናል።
በተመሳሳይ በፋሲሉ ጨዋታ ጉዳት አስተናግዶ እስከወጣበት ደቂቃ ድረስ ድንቅ እንቅስቃሴ እያደረገ የነበረው ጋዲሳ መብራቴ ትከሻው ላይ ባጋጠመው ጉዳት ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል። የፈረሰኞቹን የመጀመሪያ ግብ በጨዋታው ያስቆጠረው ጋዲሳ መብራቴ መጎዳት ለፈረሰኞቹ አስደንጋጭ ዜና ቢሆንም በተመሳሳይ መልኩ የሳልሀዲን ሰዓድ ከጉዳት አገግሞ ወደ ጨዋታ መመለሱ ደግሞ በተቃራኒው አስደሳች ዜና ሆኗል።
በእነዚህ የተጫዋቾች መተካካት የተነሳ ከሰሞኑ ለቡድኑ ውጤት ማማር የአንበሳውን ድርሻ ይወጣ በነበረው የፊት መስመር ጥምረት ላይ የሚኖሩት ሽግሽጎች በቡድኑ የማጥቃት ኃይል ምን አይነት መልክ ይኖረዋል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነው።
👉 የአቤል ያለው ለቀድሞ ክለቡ ያሳየው ክብር
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጭ ከፋሲል ከተማ ጋር 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ ፈረሰኞቹ የኃላ ኃላ መሪ የሆኑበትን ሁለተኛ ግብ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር የቻለው አቤል ያለው አስደናቂዋን ግብ ካስቆረ በኃላ ደስታውን ከመግለፅ ተቆጥቧል።
አቤል ያለው በ2009 የውድድር ዘመን ሁለተኛው ዙር ከደደቢት በውሰት ውል ፋሲል ተቀላቅሎ ከቡድኑ ጥሩ የሚባልን የስድስት ወራት ቆይታ ማድረጉ ተከትሎ በቀድሞ ክለቡ ላይ ካስቆጠራት ማራኪ ግብ በኃላ ደስታውን ሳይገልፅ ቀርቷል። በዚህም የተጫዋቹን የአስተሳሰብ ብስለት አስመልክቶ ያለፈ አጋጣሚም ነበር።
👉 ነጣቂው መስዑድ መሐመድ
ሰበታ ከተማን በክረምቱ የተቀላቀለው መስዑድ መሐመድ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቡድን ስብስብ ውስጥ በተለየ ሚና ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። አሰልጣኙ ለመጫወት በሚያስቡት የጨዋታ መንገድ ውስጥ መሀል ሜዳ ላይ ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካዮችን ከመጠቀም ይልቅ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዳዊት እስጢፋኖስን እንዲሁም በሒደት ደግሞ በሊጉ መስዑድ መሐመድን በዚህ ስፍራ ላይ በስፋት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በቀደሙት ጊዜያት ኳስን አቅልሎ መጫወት በመቻሉ፣ ግሩም በሆነ ዕይታና የማቀበል አቅሙ የሚታወቀው መስዑድ አሁን ላይ ደግሞ አዲሱ የተከላካይ አማካይነት ሚናውን በፍጥነት የለመደው ይመስላል። ምንም እንኳን የቡድኑ አጨዋወት የማጨናገፉን ተግባር በአንድ ግለሰብ ላይ ከመጣል ይልቅ እንደቡድን ክፍተቶችን በማጥበብ ላይ ያተኮረ መሆኑ ለተጫዋቹ ያገዘው ቢሆንም መስዑድ ግን በመንጠቁ ረገድ እየተሻሻለ ስለመምጣቱን የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ፍንጭ የሰጠ ነበር።
በወሳኝ የጨዋታ ቅፅበቶች ኳሶችን ከማቆረጥ በዘለለ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ኳሶችን የሚያስጥልበትና ለተከላካዮች ሽፋን የሚሰጥበት መንገድ ለቦታው አዲስ እንደመሆኑ እጅግ በተለየ ብቃት እየተወጣ ይገኛል።
👉 የጃኮ አራፋት በአአ ስታዲየም ጨዋታ መታደም
በአሰልጣኝ ደግአርግ ይዛው በተከታታይ ጨዋታዎች ከቡድን ስብስብ ውጪ ሲሆን ቆይቶ ከቡድኑ ጋር የተለያየው ቶጓዊው አጥቂ ጃኮ በትላንቱ የሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ስታዲየም መገኘቱ ስለቀጣዩ ማረፊያው ፍንጭ የሰጠ ይመስላል። በሁለተኛው ዙር ተጠናክረው ለመቅረብ ስራዎችን እየሰሩ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በቅርቡ ግዙፉን ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ንዋድኬን የአጋማሹ የመጀመሪያ ፈራሚያቸው ለማድረግ የተስማሙ ሲሆን በተጨማሪም ቀጣይ የጃኮ አራፋት ማረፊያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።
👉 የባዬ ገዛኸኝ ተፅዕኖ
መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ ምክንያት ወላይታ ድቻ ከ ባህር ዳር ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተጠባባቂ ሆኖ የጀመረው ባዬ ገዛኸኝ ተቀይሮ በመግባት ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን ችሏል። ተጫዋቹ በ35ኛው ደቂቃ የደጉ ደበበን መግዳት ተከትሎ በተደረጉ ሽግሽጎች ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ከ10 ደቂቃ በኋላ ወሳኞን የማሸነፍያ ጎል በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ አስቆጥሯል።
ዘንድሮ በጥሩ አቋሙ ላይ የሚገኘው ባዬ በፕሪምየር ሊጉ 7 ጎሎች ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ይህም ከቡድኑ አጠቃላይ ጎሎች ግማሹን መሆኑ ነው። ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች ቡድኑ ላሳየው መሻሻልም ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዱ ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ