በግብፅ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያዊው ሽመልስ በቀለ የሚጫወትበት ክለብ ፔትሮጀት ትላንት ማምሻውን ድል ቀንቶታል፡፡ ሽመልስ በ18ኛ ሳምንት ጨዋታ ፔትሮጀት ከአል መስሪ ጋር ያለግብ አቻ በተለያየበት ጨዋታ የተቀያሪ ወንበር ላይ ለመቀመጥ የተገደደ ሲሆን ትላንት ግን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ከወራት በኃላ ለመመለስ ችሏል፡፡
ፔትሮጀት ሰሞሃን 3-1 በረታበት ጨዋታ ሽመልስ ሙሉ 90 ደቂቃ ተጫውቷል፡፡ በጨዋታው ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው ሽመልስ በ51ኛው ደቂቃ ከአህመድ ጋፍር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት ቀይሯል፡፡ ይህች ግብ ለሽመልስ በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግቡ ነች፡፡ የፔትሮጀትን ቀሪ የድል ግቦች በአስደናቂ ብቃቱ ላይ የሚገኘው አህመድ ጋፍር እና መሃመድ ራጋብ እስቆጥረዋል፡፡ ለሰሞሃ ከዛማሌክ በውሰት የመጣው ኢብራሂም ሳላ ኳስን ከመረብ አዋህዷል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ የሰሞሃ አሰልጣኝ ሚሚ አብደልራዛክ ራሳቸውን ከአሰልጣኝነት መንበሩ አንስተዋል፡፡ በ2015 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ተፋላሚ የነበረው ሰሞሃ ዘንድሮ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተስኖታል፡፡
የሽመልስ በቀለ ግብ ለመመልከት ይህንን ሊንክ ይጫኑ፡- https://m.youtube.com/watch?v=xs9qAZgENlk&feature=youtu.be