የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ላይ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ጥሩ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉትን በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል።
* ምርጫው የሚከናወነው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተሮች እንዲሁም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ባለሙያዎች ለተጫዋቾች በሚሰጡት ነጥብ መነሻነት ነው።
* ምርጫው ተጫዋቾች በዕለቱ በተሰለፉበት ጨዋታ ላይ ባሳዩት ብቃት ላይ የተመረኮዘ ነው።
* ፎርሜሽኖች እና የተጫዋቾች ቦታዎች በምርጫው የተካተቱት ተጫዋቾችን ባማከለ መልኩ በየጊዜው ሊቀያየሩ ይችላሉ።
አሰላለፍ ፡ 4-2-3-1
ፍቅሩ ወዴሳ (ሲዳማ ቡና)
ሲዳማ ቡና ወደ ወልቀጤ ተጉዞ 1-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ፍቅሩ ጥሩ መንቀሳቀስ ችሏል። ለወትሮው በርካታ ጎሎች ሲቆጠርበት የነበረው የኋላ ክፍልን በመምራት ቡድኑ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ጎል ሳይቆጠርበት እንዲወጣ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተው ፍቅሩ በተለይ ባለሜዳዎቹ ጫና ፈጥረው በተንቀሳቀሱበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሞከሩበትን ሙከራዎች በማክሸፍ ጥሩ ጊዜ አሳልፏል።
ሥዩም ተስፋዬ (መቐለ 70 እንደርታ)
በዚህ ሳምንት ድንቅ እንቅስቃሴ ካደረጉ ተጫዋቾች አንዱ ነው። መቐለ ሀዋሳን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው ይህ የመስመር ተከላካይ በእንቅስቃሴም ሆነ ቡድኑን በመምራት ወሳኝነቱን አስመስክሯል። ተጫዋቹ ከሁለቱ ጎል የሆኑ ኳሶች በተጨማሪ ከመስመር በሚያሻግራቸው ኳሶች ለበርካታ የግብ ዕድሎች መፈጠር ምክንያት ነበር።
ወንድሜነህ ደረጀ (ኢትዮጵያ ቡና)
የተረጋጋው የኢትዮጵያ ቡናው የመሐል ተከላካይ ወንድሜነህ ደረጀ በሰበታው ጨዋታ ወሳኝ የተጋጣሚ የማጥቃት ሒደቶችን በማቋረጥ እና አልፎ አልፎ ከፊቱ የሚኖሩ ክፍት ሜዳዎችን በመጠቀም የማጥቃት ሒደቶችን ለማስጀመር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በጫናዎች ውስጥ ሆኖ ኳሶችን ለመቀበልና ለማቀበል ሲቸገር የማይስተዋለው ወንድሜነህ ኃላፊነቶችን ለመውሰድ ያለው ድፍረትና ዝግጁነት የሚያስደንቅ መሆኑን በትላንቱ ጨዋታ አስመስክሯል።
ንጋቱ ገብረሥላሴ (ጅማ አባ ጅፋር)
ንጋቱ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ቢሆንም፤ ጅማ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታም በአማካይነት ቢጀምርም በ7ኛው ደቂቃ ተከላካዩ አሌክስ አሙዙ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱን ተከትሎ የመጀመርያውን አጋማሽ ወደ ኋላ አፈግፍጎ በመጫወት የተከላካይነት ሚና በብቃት መወጣት ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ተከላካዩ ከድር ኸይረዲን ተቀይሮ ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ ደግሞ ወደ አማካይነቱ ተመልሶ ለተከላካዮች በሚገባ ሽፋን በመስጠት በተጫዋች መጉደል ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት መድፈን ችሏል። በዚህም በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ 11 በተከላካይ ሥፍራ ላይ ተካቷል።
ጀሚል ያዕቆብ (ጅማ አባ ጅፋር)
የመስመር ተከላካዩ ቡድኑ ድሬዳዋን ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ሚዛናዊ የሆነ የማጥቃትም እና የመከላከል ተግባር በመከወን ጥሩ ቀን አሳልፏል። ጀሚል በተለይ ድሬዎች ጫና ለመፍጠር ሲጠቀሙበት በነበረው መስመር ላይ የነበረው የመከላከል ሚና መልካም የነበረ ሲሆን በፈጣን የመስመር ሽግግር የመልሶ ማጥቃትን ለማስጀመር ሲያደርግ የነበረው ጥረትም ጥሩ የሚባል ነበር።
ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ (መቐለ 70 እንደርታ)
ከአንድ ጨዋታ በኋላ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ተመልሶ መቐለ በጥሩ ብቃት ሀዋሳ ከተማን ሲያሸንፍ ትልቅ ድርሻ የነበረው ሙሉጌታ በጨዋታው አንድ ግብ ስያስቆጥር በሁለቱም አጋማሾች የተሰጡትን የተለያዩ ሚናዎች በአግባቡ ተወጥቷል። አማካዩ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲካተትም ይህ ለሁለተኛ ጊዜው ነው።
ታፈሰ ሰለሞን (ኢትዮጵያ ቡና)
የጥሩ ዕይታ ባለቤቱ ታፈሰ ኢትዮጵያ ቡና ከሰሞኑ ጨዋታዎች አንፃር መሻሻልን ባሳየት የትናንቱ ጨዋታ የማጥቃት ጨዋታውን በመምራት ረገድ አይነተኛ ሚና ነበረው። ከኃላ የሚመጡትን ኳሶች በአስገራሚ ብቃት ሲያሰራጭ የነበረው ታፈሰ በተለይ በአቤል ከበደ በግራ መስመር በረጃጅም ኳሶች ያገኝበት የነበረው መንገድ ልዩ ነበር። ቡድኑ ለፈጠራቸው በርካታ የጎል ዕድሎችም መነሻ ነበር።
ቡልቻ ሹራ (አዳማ ከተማ)
በእሁዱ ጨዋታ ምንም እንኳን የአዳማ ከተማ የአማካይ ክፍል እምብዛም ጫና ሳይደርስበት ተጋጣሚውን መቆጣጠር ቢችልም በማጥቃቱ ረገድ ውጤታማ እንዲሆን የመስመር አጥቂዎቹ እገዛ ከፍ ያለ ነበር። በዚህም ረገድ ቡልቻ ሹራ የአካል ብቃቱ እና ፍጥነቱን በመጠቀም ከመሀል ክፍሉ የሚደርሱ ኳሶችን ተጠቅሞ ፊት ላይ ክፍተቶችን በመፍጠር በኩል ጥሩ 90 ደቂቃ አሳልፏል። ቦታ በመቀያየርም የወልዋሎን ተከላካይ ክፍል ሲረብሽ ይታይ ነበር። የቡድኑን የበላይነት ያሰፋችውን ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥርም የግል ብቃቱ ጎልቶ የታየ ሲሆን በወቅቱ የነበረበት የፊት አጥቂነት ቦታ በጨዋታው ለነበረው የተለዋዋጭነት ሚናው ማስረጃ ነበር።
ጌታነህ ከበደ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ጌታነህ ሁሉ ነገሩን ለፈረሰኞቹ መስጠቱን በየጨዋታዎቹ ቀጥሎበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከነማ ጋር ባደረገው የሊጉ ወሳኝ ጨዋታ ወቅት የቡድኑን የመጥቃት ሚዛን በመጠበቅ እና ኳሶችን በተገቢው መንገድ በማሸራሸር እንዲሁም ከአጥቂ ጀርባ የተሰጠውን አዲሱን ሚና በአግባቡ ሲወጣ መመልከት ችለናል። ከዚህ ባሻገር አቤል ያለው ላስቆጠራት ሁለተኛ ጎል የእርሱ ድርሻ የጎላ ነበር።
አቤል ያለው (ቅዱስ ጊዮርጊስ)
ፈጣኑ አጥቂ አቤል ያለው በቅርብ ሳምንታት በየጨዋታዎቹ ጎል ማስቆጠርን ተያይዞታል። ፈረሰኞቹ በሚያደርጉት ግስጋሴ ውስጥም የወጣቱ አጥቂ ሚና የጎላ እየሆነ መጥቷል። በተጠባቂው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጭ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የዐፄዎቹን ተከላካይ ሲረብሽ የዋለው አቤል አንድ ጎል ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ጋዲሳ መብራቴ ላስቆጠራት የመጀመርያ ጎልእ አስተዋፅኦ አድርጓል። ከጨዋታ ጨዋታ ድንቅ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው አቤል በሶከር ኢትዮጵያ ለተከታታይ ሦስተኛ ሳምንት ምርጥ 11 ውስጥ ሊካተት ችሏል።
ኦኪኪ ኦፎላቢ (መቐለ 70 እንደርታ)
ከቀዝቃዛው አጀማመር በኋላ ወደ ጥሩ ብቃት ተመልሶ ባለፈው ሳምንት ከድንቅ እንቅስቃሴ ጋር ሐት-ትሪክ የሰራው ይህ ናይጀርያዊ አጥቂ ከሀዋሳ ጋር በነበረው ጨዋታ ሦስት ግቦች ከማስቆጠሩም በተጨማሪ ድንቅ እንቅስቃሴ አድርጓል። በጨዋታዎች ከሚያደርጋቸው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በተጨማሪም ወሳኝ የማሸነፍያ ግቦች ማስቆጠር የጀመረው ይህ ግዙፍ አጥቂ በሶከር ኢትዮጵያ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ሲገባ ለሁለተኛ ጊዜው ነው።
ተጠባባቂዎች
ዳንኤል አጃይ (ሰበታ ከተማ)
አዩብ በቀታ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ተስፋዬ አለባቸው (ወላይታ ድቻ)
አማኑኤል ጎበና (አዳማ ከተማ)
በረከት ደስታ (አዳማ ከተማ)
ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)
ስንታየው መንግሥቱ (ባህር ዳር ከተማ)
© ሶከር ኢትዮጵያ