የፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫)- አሰልጣኞች ትኩረት

በዚህ ሳምንት ትኩረት ሳቢ የነበሩ አሰልጣኝ ተኮር ጉዳዮች እና ዐበይት አስተያየቶችን እነሆ!

👉 ደለለኝ ደቻሳ ለቋሚነት?

ወላይታ ድቻዎች ከአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ጋር መለያየታቸውን ተከትሎ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ቡድኑን የተረከበው ወጣቱ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳ ለቡድኑ አስደናቂ መሻሻል በግንባር ቀደምነት ይጠቃሳል።

አሰልጣኙ ቡድኑን እየመራ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በሀዋሳ ከተማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ውጭ የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ድል በማድረግ የፕሪምየር ሊግ የሥራ ማኅደራቸውን በመልካም ውጤቶች እየከፈቱ ይገኛሉ።

በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በተጣለው መሠረት ላይ ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኙ ከተጫዋቾቻቸው የተሻለውን ብቃት አውጥቶ በመጠቀም ላይ እየተሳካላቸው ሲሆን በተለይ ከተስፋ ቡድኑ በቅርብ ዓመታት ያደጉትና የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑት በረከት ወልዴ፣ ቸርነት ጉግሳ እና እዮብ ዓለማየሁን ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው የተሻለ ተጠቃሚ ያደረጋቸው ይመስላል።

አሰልጣኙ ቡድኑን ከተረከቡ ወዲህም የተለያየ መልክ ሲኖራቸውም ይስተዋላል። በመጀመሪያ አጋማሽ በተቻላቸው አቅም አጥቅተው ግቦችን ለመያዝ የሚሞክረው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥንቃቄን ላይ በማተኮር ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል ይህም እንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።

አሰልጣኙ ቅጥራቸው ሲፈፀም እስከ ውድድር ዘመኑ አጋማሽ ቡድኑን እንደሚመሩ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም እያስመዘገቡት ከሚገኘው ወቅታዊ ውጤት አንፃር ኃላፊነቱን በቋሚነት የማግኘታቸው ነገር ሚዛን የሚደፋ ይመስላል።

👉 ኢትዮጵያ ቡና ተለዋዋጭ እየሆነ ይሆን?

ከዚህ ቀደም በነበሩት አመታት በአሰልጣኛ ካሳዬ እና ሊከተሉት በሚያስቡት የአጨዋወት መንገድ ዙርያ በርከት ያሉ ሀሳቦች ይደመጡ ነበር። በተለይ አጨዋወቱ ዙርያ ያሉ ሀሳቦች ሲጠቀለሉ “ኳስን ከኃላ በመመስረት በርከት ባሉ አጫጭር ቅብብሎች ወደ ግብ መድረስ” የሚለው ድፍን ያለ ሀረግ በተወሰነ መልኩ የጨዋታ ሀሳቡን እንደሚገልፅ ተደርጎ ሲቀርብ ይደመጣል። ምንም እንኳን አሰልጣኙ በቅጥራቸው ወቅት በነበሰው ይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደጠቆሙት በ1995/6 ከነበረው የጨዋታ አስተሳሰብ መነሻ እንቅስቃሴው ተመሳሳይ ሆኖ በሂደት የተሻሻሉና የተጨመሩ ነገሮች ስለመኖራቸው መናገራቸው ይታወሳል።

ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጀምሮ ቡድኑ በሒደት በተጋጣሚዎች አቀራረብ መነሻ በማድረግ በርከት ያሉ ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ እየተስዋለ ይገኛል። ምንም እንኳን አሰልጣኙ እነዚህ ረጃጅም ኳሶች የተጋጣሚን ጫና በተወሰነ መልኩ ለማምለጥና ወደሚፈልጉት እንቅስቃሴ ለመግባት ተጫዋች ረጃጅም ኳሶችን መጠቀማቸውን እንደማይቃወሙ ሲናገሩ ቢደመጥም ይህ ሂደት በተለይ በትናትናው ጨዋታ ላይ ተደጋግሞ ሲደረግ ተስተውሏል።

ተጋጣሚያቸው ሰበታ ከተማ በሜዳው የላይኛው ክፍል በቁጥር በርከት ብለው ከፍ ያለ ጫናን (high press) ለማድረግ ይሄዱበት የነበረው ጥረት ቅንጅት የሚጎድለው ከመሆኑና ከየሰበታ ተከላካዮች ወደ መሀል ሜዳ መጠጋታቸውን ተክትሎ ተከላካዮች ጀርባ የሚኖረውን ጥልቀት ለማጥቃት በማሰብ በተለይም አቤል ከበደ በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል ተደጋጋሚ የአግድመት ኳሶች ሲጣሉ ይስተዋል ነበር።

ይህም በቀደመው ጊዜ የእነ ካሳዬን የጨዋታ መንገድ ከኳስ ቁጥጥርና አጫጭር ቅብብሎች ጋር የማቆረኙት ተለምዶአዊ አስተሳሰብ ቡድኑ በተወሰነ መልኩ እንደ ሁኔታው የሚለዋወጥ መልክ ያለው ቡድን እየሆነ የመጣ ይመስላል።

👉 ያለ አሰልጣኙ የተጫወተው ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በሀዘን ምክንያት ሳይመሩ ቀርተዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት ቡድኑን በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ የነበሩት ምክትል አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ ቡድኑን መርተዋል።

ቡድኑ በጨዋታው ዋና አሰልጣኙ ካለመኖራቸው በተጨማሪ በጊዜ ጎል አስቆጥረው በሚመሩበት ወቅት አንድ ተጫዋች በቀይ ካርድ አጥተው በቅፅበት የአቻነት ጎል መቆጠሩ ጨዋታውን እንደሚያከብድባቸው ቢገመትም በድጋሚ ወደ መሪነት የሚመልሳቸውን ጎል በማስቆጠር ለረጅም ደቂቃዎች መሪነታቸውን አስጠብቀው መውጣታቸው የሚደነቅ ነው። በተለይ አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ የተከላካይ ተጫዋች መውጣቱን ተከትሎ በተለምዶ እንደሚደረገው የአጥቂ ባህርይ ያለው ተጫዋች በማስወጣት ተከላካይ ያስገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በሜዳ ውስጥ የተጫዋች ሚና ሽግሽግ ያደረጉበት ውሳኔ ትኩረት የሚስብ ነበር።

👉 ዐበይት አስተያየቶች

* ፀጋዬ ኪዳነማርያም ሀዲያ ሆሳዕና የተረከቡበት በፈታኝ ሰዓት ስለመሆኑ

“በፈታኝ ሰዓት ነው ቡድኑን የተረከብኩት፤ ፈተናውም በአግባቡ ለመወጣት ጠንክሬ እሰራለሁ። ከተጫዋቾቼ፣ ከአመራር እና ከቡድናችን ደጋፊዎች ጋር ተባብሮ በድምር ጥሩ ስራ መስራት ነው እቅዳችን። ዋና ዓላማችን ያሉንን ክፍተቶች አርመን በሁለተኛው ዙር ደረጃችንን ማሻሻል ነው። ደረጃችን ትንሽ ወረድ ብሏል፤ ሆኖም የማይሻሻልበት ምንም ምክንያት የለም። በሁለተኛውን ዙር በቂ የዝግጅት ጊዜ ስላለን የተቻለንን ሁሉ አድርገን ቡድኑን በሊጉ ላይ ማቆየት ነው።”

* ካሣዬ አራጌ ቡድን በሰበታው ጨዋታ በተለይ በርካታ ረጃጅም ኳሶችን ስለመጠቀማቸው

“ተጋጣሚዎቻችን ይዘው ከሚመጡት ነገር አንፃር እኛ የምናስባቸው ነገሮች አሉ። እስካሁን ድረስ አብዛኛዎቹ የገጠምናቸው ቡድኖች በሶስት የተለያዩ መንገዶች ይቀርባሉ። ነገርግን ባለፈው ሳምንት ወልቂጤዎች በተለየ (አራተኛው መንገድ) ቀርበዋል። ስለዚህ እነዚህን በመንተራስ እኛ ሁለተኛ አማራጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ተጋጠሚያችን ሁኔታ እስከ አራተኛ አማራጭ ድረስ ይኖሩናል ማለት ነው። ረጃጅም ኳሶች ከዚህ በፊት የሚደረጉ ነገሮች ናቸው። ምናልባት ዛሬ አንዳንዶቹ ረጃጅም ኳሶች ውጤታማ ስለነበሩ በዛ መልኩ ለመጠቀም ያሰብን ይመስል የነበረው እንጂ ከዚህ ቀደምም ይደረጉ ነበር። ነገርግን የቅብብል ስህተቶች ስለነበሩባቸው ዛሬ የተለየ መሰለ እንጂ በፊትም የነበረ ነው።”

* የድሬዳዋው ጊዜያዊ አሰልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን ስለቁጥር ብልጫና ሰዓት ማባከን

“ቁጥር ብልጫው እንኳን ችግር የለውም። አንድ ቡድን ስነልቦናውም ይጠነክራል። የወጣበት ቁጥር ዞሮ ዞሮ ሰበብ ሊሆን አይችልም፤ የአንድ ሰው ቁጥር ብልጫውን መጠቀም ነበረብን። ከእረፍት መልስ ግን ኳስ አልተጫወትንም እነሱ ሲተኙ ነው የዋሉት፤ የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ የትም መድረስ አለመቻሉ ነው። ሰው ሲተኛ በዛው ተጠናቀቀ።”

* የስሑል ሽረው ምክትል አሰልጣኝ መብራህቶም ፍስሀ ስለቡድናቸው በዚህኛው ሳምንት ደክሞ መቅረብ መንስኤ

ጨዋታው በቡድናችን በኩል ከባለፉት ሳምንታት የደከመ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። ምክንያቱም በተጫዋቾቻችን ጫናዎች አሉ። ጉዳት ያለባቸው ፣ ከነጉዳታቸው ወደ ጨዋታ የገቡ እና በቅጣት ያልገቡ ተጫዋቾች አሉ። ሌላ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ያደረገናቸው አስገዳጅ ቅያሬዎች ጨዋታውን በፈለግነው መንገድ እንዳንቀጥለው አድርገውናል። በዛ ምክንያትም እንደባለፉት ጨዋታዎች ብዙ ዕድሎች መፍጠር አልቻልንም። በአጠቃላይ ድካሞ እና ያሉት አንዳንድ የጠቀስኳቸው ነገሮች ጥሩ እንዳንቀሳቀስ አድርገውናል።”

* የአዳማው ምክትል አሰልጣኝ በጨዋታው ስላደረጉት ታክቲካዊ ለውጥና የደሞዝ ጉዳይ

“በመጀመሪያ በሦስት ተከላካይ አድርገን ፉዓድ ያለቦታው ቢሆንም እየሄደ እንዲያጠቃ ነበር ያሰብነው። የለወጥነውም በታክቲካዊ ምክንያት እንጂ ጥሩ ሳይሆን ቀርቶ አልነበረም። እውነተኛ የመስመር ተከላካይ ለመጠቀም በማሰብ ነበር ለውጡን ያደረግነው።

“አሁን ጥሩ ነው፤ መስመር ይዟል። ለዛም ነው በዚህ ሳምንት መደበኛ ልምምዳችንን ስናደርግ የቆየነው። ከአመራሩም ጥሩ ነገር ስላለ እንደሚስተካከል እርግጠኛ ነኝ። ያም ስለሆነ ነው ተጨዋቾቹም ተነሳሽነታቸው ጥሩ የሆነው ፤ የሚቀጥለው ሳምንት ላይ ደግሞ ሁሉ ነገር እንደሚያልቅ ቃል ተገብቷል።”

* የመቐለ ምክትል አሰልጣኝ ጎይቶም ኃይለ በቅዳሜ ጨዋታ በተጫዋቾቻቸው ላይ ስለነበረው መነሳሳትና የሁለተኛ ዙር እቅድ

“ተጫዋቾቻችን ላይ የነበረው መነሳሳት በጣም ጥሩ ነበር። በጥሩ ፍላጎት ነበር የተጫወቱት። የአሰልጣኞች ቡድናችንም ሳምንቱን ሙሉ በጥሩ መንገድ ነበር ለጨዋታው ያዘጋጀናቸው። በአጠቃላይ ውጤቱ ጥሩ ነው። አንደኛው ዙር እየተገባደደ ነው። ለሁለተኛው ዙር ደግሞ ጠንክረን ነው የምንቀርበው። ከመሪዎቹ ብዙም አልራቅንም ካሁን በኃላ የምናደርጋቸው ጨዋታዎች ግን ወሳኝነት አላቸው።”

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ