የፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በፕሪምየር ሊጉ ሌሎች ትኩረት ሳቢ የነበሩ የሳምንቱ ጉዳዮችን እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

👉 የተጫዋቾች ዲሲፕሊን እና ካርዶች

በዚህ ሳምንት አራት የቀይ ካርዶች ተመዘዋል። ይህም የዘንድሮው ሊግ ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛው ሆኗል። በአንድ ጨዋታ 11 የማስጠንቀቂያ ካርድ የታየበት ጨዋታ የታየውም በዚህ ሳምንት ነበር።

ካርድ የሚሰጡባቸው ምክንባቶች መለያየት (ቴክኒካዊ ጥፋቶች እና የዲሲፕሊን ጥሰት ዋነኞቹ ናቸው) እንዲሁም የሚመዘዙት ካርዶችን ብዛት በደፈናው ተመልክተን የተጫዋቾችን የዲሲፕሊን ሁኔታ መፈረጅ ከባድ ቢሆንም በተናጠል ምክንያቶችን ስንመለከት ግን የተጫዋቾቻችንን፣ የቡድን አባላትን እና አጠቃላይ እንደ ቡድን ያለብንን ደካማ የዲሲፕሊን ሁኔታ የሚያመለክቱ ናቸው።

በዚህ ሳምንት ከተሰጡት አራት የቀይ ካርዶች የጅማው አሌክስ አሙዙ ብቻ በቴክኒካዊ ጥፋት የተመለከተ ሲሆን አለልኝ አዘነ ከዳኛ ጋር በተገባው ሰጣ ገባ፣ ደስታ ደሙ እና ሽመክት ጉግሳ ደግሞ እርስ በርስ በፈጠሩት ግብግብ የተመለከቱት ነው። በአጠቃላይ ዘንድሮ ከታዩት ቀይ ካርዶችም አመዛኞቹ ከአላስፈላጊ ግብግብ የመነጩ መሆኑን ስንመለከት ይህን ሀሳብ ያጠናክርልናል።

ከቀይ ካርዶች ጋር በተያያዘ ለወትሮው የጨዋታው ግለት በሚጨምርባቸው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ የሚታየው ቀይ ካርድ አሁን አሁን ገና ጨዋታው በቅጡ ቅርፅ ሳይዝ መሆኑ አስገራሚ ያደርገዋል። አሌክስ አሙዙ (8′)፣ ዲዲዬ ለብሪ (10′)፣ አለልኝ አዘነ (26′)፣ አብርሀም ታምራት (26′) እና ወንድወሰን አሸናፊ (28′) የመሳሰሉ ተጫዋቾች ከሜዳ የተሰናበቱበት ሰዓትን ተመልክተን ቁጥር የጎደለባቸው ቡድኖች ምን ያህል ችግር ውስጥ እንደገቡ መገመት አያዳግትም።

በቢጫ ካርዶች ረገድም በእንቅስቃሴ መሐል በሚሰሩ ጥፋቶች ከሚሰጡት ካርዶች ይልቅ በሰዓት ማባከን፣ ከዳኛ ጋር በሚፈጠር ሰጣ ገባ እና በግድ የለሽነት በሚሰሩ ጥፋቶች የሚመዘዙት ያመዝናሉ። እነዚህ ሁኔታዎች የውድድር ዓመቱ በገፋ ቁጥር የመደጋገም ዝንባሌዎች እያሳየ መምጣቱ አይቀሬ በመሆኑ ከፍተኛ ውጥረት በሚኖርባቸው የሁለተኛ ዙር መርሐ ግብሮች ላይ የጨዋታዎችን መንፈስ እንዳይረብሽ የሚያሰጋ ነው።

👉 የስታዲየም ፀጥታ አጠባበቅ…

ከወልቂጤ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሳምንቱ አጋማሽ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታ በርከት ያሉ ተጓዥ የወልቂጤ ደጋፊዎች ትኬት ቆርጠው ወደ ስታዲየም መግባት አለመቻላቸውን መነሻ በማድረግ የክለቡ ደጋፊዎች በአመራሮቻቸው ላይ ያሰሙት ተቃውሞ መስመር ስቶ አስለቃሽ ጭስ ተኩስና ቁስ ውርወራዎች የተከተሉ ሲሆን በሰዎች ላይ ጉዳት እንዲደርስም ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ከሲዳማ ቡና ደጋፊዎች ጋር በተፈጠረ ችግር የድንጋይ መወራወር ደጋፊዎች ላይ የመፈንከት አደጋዎች ሲደርሱ ተስተውሏል።

በሌላኛው የሰኞው መርሐ ግብር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ሰበታ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና አቻ በተለያዮበት ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኞች ቡድን አባላትና ተጠባባቂ ተጫዋቾች በዳኛው ላይ ተቃውሟቸውን ለማሰማት ከወንበራቸው በተነሱበት ወቅት በፀጥታ አስከባሪዎች ከስልጣናቸው ወሰን ውጭ አዋክበው ወደ ወንበራቸው እንዲመለሱ የተሞከረበት አግባብ እንዲሁ ሌላው ትኩረት የሚስብ አጋጣሚ ነበር።

በርካታ ችግሮች የሚነሱበት የስታዲየም የደህንነት አጠባበቅ ስርዓታችን ነፀብራቅ የሆኑት ሁለቱ ክስተቶች በቀጣይ መታረምን የሚሹ ናቸው። እግርኳስ ለተጫዋቾቹም ሆነ ለተመልካቾቹ በስሜት የተሞላ ስፖርት እንደመሆኑ የፀጥታ አካላት ይህን ታሳቢ ያደረገ እንዲሁም ስለ ስታዲየሞች ባህሪና አጠቃላይ መረጃዎች በሌላቸው ሁኔታ መሰል ህዝብ የተሰበሰቡባቸውን ሁኔታዎች እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው በቂ እውቀት በሌላቸው ሁኔታ መሰል ችግሮች በቀጣይነትም መከሰታቸው አይቀሬ በመሆኑ የስታዲየም ፀጥታ አጠባበቅ ዙሪያ የፀጥታ አካላት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ስልጠና ሊሰጣቸው ይገባል።

👉 ከተመልካች ነፃ የነበሩት የአዲስ አበባ ስታዲየም ክፍሎች

በተለዋጭነት ባስያዙት የአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታዎችን እያከናወኑ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች ሰኞ ኢትዮጵያ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታ የተወሰኑ የአዲስ አበባ ስታዲየም ክፍሎች ከተመልካች ነፃ ሆነው አስተውለናል።

ለወትሮው ሰበታ ከተማዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የተወሰኑ የስታዲየም በሮች ዝግ የመሆናቸው ነገር እንግዳ ክስተት ባይሆንም ክለቡ እንደ ትላንቱ አይነት በርከት ያሉ ደጋፊዎች ሊገኙበት በሚችሉት ጨዋታ ሁሉንም በሮች ክፍት በማድረግ የጨዋታ እለት ገቢ መጠናቸውን ያስድጋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሰበታዎች በቀደመው አሰራራቸውን ለመቀጠል መርጠዋል።

ውሳኔው ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ቁጥር መብዛት ጋር ሊፈጠር የሚችለውን የደጋፊዎች ጫና በተወሰነ መልኩ በመቀነስ ረገድ የታቀደ መሆን ስለመሆኑ ማወቅ ባይቻልም በሀገሪቱ ስታዲየሞች በተለምዶ ለባለሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ላሉ ቡድኖች የተገደበ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ቀድሞ ስታዲየም የተገኘ ተመልካች የሚስተናገድበት በመሆኑ ከፍተኛ የደጋፊ ቁጥር ያላቸው ቡድኖች ስታዲየሙን ሲሞሉት እንደመስተዋሉ የሰኞው ሁኔታ ለበርካቶች ግርታን የፈጠረ ጉዳይ ሆኖ ታይቷል።

👉  የቁጥር ብልጫ አጠቃቀም ጉዳይ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋቾችን በካርድ የሚያጡ ቡድኖች እና ሙሉ ተጫዋቾችን የያዙ ቡድኖች መካከል በሚደረጉ ጨዋታዎች ወቅት በሁለቱ ቡድኖች መካከል ይህ ነው የሚባል የጎላ ልዩነት ሲታይ አይስተዋልም።

ለአብነትም በዚህኛው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን ሲያስተናግድ በጨዋታው ገና በ8ኛው ደቂቃ የመሀል ተከላካያቸው አሌክስ አሙዙን በቀይ ካርድ ያጡት ጅማ አባ ጅፋሮች እስከ እረፍት ድረስ ተፈጥሯዊ የተከላካይ ተጫዋችን በምትኩ ሳይተኩ የተጫዋቾች የሚና ሽግሽግ ማድረግ ችለዋል። ከ80 ደቂቃ በላይ በጎዶሎ ተጫዋቾች ተጫውተውም ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል። በተመሳሳይ ባሳለፍነው ሳምንትም ድሬዳዋ ከተማ በሜዳው ሽረን ጋብዞ አቻ በተለያየበት ጨዋታ ሽረዎች እየተመሩ ባለበት ወቅት አንድ ተጫዋቾች በቀይ ቢያጡም በ10 ተጫዋቾች መጫወት ቀጥለውኋኃ ላይም ጎል አስቆጥረው አቻ መለያየት ችለዋል።

ምንም እንኳን አሰልጣኞቹ በሚሰጡት ድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ ወቅት መሰል የተጫዋቾች መጉደል ቀሪ ተጫዋቾች ላይ በሚፈጥረው ከፍተኛ መነሳሳት እና ለመከተል በሚያስቡት የመከላከል አጨዋወት ምክንያት ትርጉም እንደማይኖረው ተደርጎ ቢገለፅም በሜዳ ላይ ያለው የቁጥር ብልጫን ግን በአግባቡ መጠቀም እየተቻለ ጠቀሜታውን በሚሉት ደረጃ መንኳሰሱ አግባብ አይደለም።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ