ወልዋሎ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል

ላለፉት ቀናት ቢጫ ለባሾቹን ለማሰልጠን ከክለቡ የበላይ አካላት ጋር ንግግር ሲያደርጉ የቆዩት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደዮርጊስ የወልዋሎ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል።

ከክለቡ ጋር ንግግር ከጀመሩ በኃላ የቡድኑን እንቅስቃሴ በቅርበት እየተከታተሉ የቆዩት አሰልጣኝ ዘማርያም ክለቡ በአዳማ ከተማ ሽንፈት ሲገጥመው በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታውን የተከታተሉ ሲሆን ከቀጣይ ሳምንት በኋላ በሚከፈተው የዝውውር መስኮትም ቡድኑን ለማሻሻል ዝውውሮችን ይፈፅማሉ ተብሎ ይገመታል።

ከዚህ ቀደም በፋሲል ከነማ፣ ወልዲያ እና ጅማ አባ ጅፋር መስራት የቻሉት አሰልጣኙ ወልዋሎን ከወራጅ ቀጠናው አውጥቶ በሊጉ የማቆየት ከባድ ኃላፊነት ተረክበዋል።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ በዚህ ወቅት የአሰልጣኝ ቅያሪ ያደረጉት ወልዋሎዎች በ2010 ከብርሀኔ ገብረእግዚአብሔር ጋር ተለያይተው ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ሲቀጥሩ ባለፈው ዓመትም ፀጋዬን በዮሐንስ ሳህሌ መተካታቸው ይታወሳል።

በክረምቱ እጅግ በርካታ ተጫዋቾች ያስፈረሙት ወልዋሎዎች እምብዛም ግልጋሎት ካልሰጧቸው ተጫዋቾች ጋር በስምምነት እየተለያዩ ሲሆን በምትካቸውም በቅርቡ በተከፈተው የዝውውር መስኮትም ተጫዋቾች ያስፈርማሉ ተብሎ ይታሰባል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ