የሐውዜኑ ግብ ጠባቂ ናኦድ ገብረእግዚአብሔር የምላስ መዋጥ አደጋ የደረሰበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጫዋችን ሕይወት አትርፏል።
ከቀናት በፊት በአንደኛ ሊግ ጨዋታዎች አንዱ በነበረው የሐውዜን እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አስደንጋጭ ክስተት አስተናግዶ ነበር። በጨዋታው እንቅስቃሴ ውስጥ አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጫዋች ከተጋጣሚ አጥቂ ጋር ተጋጭቶ ራሱን በመሳቱ የምላስ መንሸራተት እና የመተንፈሻ ትቦ መዘጋት አጋጥሞት ነበር። ሆኖም የተቃራኒ ቡድን ግብ ጠባቂ ሆኖ የተሰለፈው የሐውዜኑ ግብ ጠባቂ ናኦድ ገብረእግዚአብሔር ደርሶ የአዲስ አበባ ፖሊሱን ተከላካይ ህይወት ታድጓል።
ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገውና የተጫዋቹን ሕይወት የታደገው ግብ ጠባቂ ከአራት ዓመት በፊትም ተመሳሳይ አደጋ በራሱ ላይ ደርሶበት እንደነበር የገለፀ ሲሆን ሁኔታውም ከባድ እንደነበር ገልፅዋል። “ተጫዋቹ ምላሱን ነው የዋጠው ሲሉ ሰምቼ ነው ተቃራኒ ጎል ድረስ ሮጬ ሄጄ ሕይወቱን ለማዳም የሞከርኩት፤ ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። እንደሚታወቀው የኛ ሊግ በቂ ትኩረት ስለማይሰጠው አፋጣኝ ህክምና የማግኘት ዕድልህ የጠበበ ነው። ሁሉም በሁኔታው ተደናግጦ ስለነበር የሚችለው ነገር ሁሉ ማድረግ አቅቶት ነበር። እኔ ግን ተመሳሳይ አደጋ ደርሶብኝ ስለነበር ቶሎ ጓንቴን አውጥቼ የምችለው እርዳታ አደረግኩ፤ የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖም ሕይወቱን አትርፌዋለው። ” ብሏል።
ተጫዋቹ ስለ ከባዱ ሁኔታ ሲያስረዳም እንዲህ ይላል። “ደጋፊውም፤ ሜዳ ላይ የነበረው ተጫዋችም በሁኔታው ተደናግጦ ማልቀስ ጀምሮ ነበር። ክለቦች ተመሳሳይ ችግር እንደሚያጋጥም አውቀው በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው።”
ብዙም የሚድያ ትኩረት እና በቂ የሕክምና ድጋፍ በማይገኝበት ሊግ ላይ ተመሳሳይ አስከፊ ጉዳቶች በርካታ ቢሆኑም በየጊዜው ችግሩ ሲቀረፍ አይታይም።
ከዚህ ቀደም እነዲህ አይነት ክስተቶች በኢትዮጵያ እግርኳስ በተደጋጋሚ ያጋጠሙ ሲሆን የአሁኑ የሰበታ አማካይ በኃይሉ አሰፋ ለደደቢት በሚጫወትበት ወቅት የሙገሩ ዳንኤል መኮንን፤ እንዲሁም ፌዴራል ዳኛ አዳነች ታደሰ በዳኘችበት ጨዋታ ቅድስተ ማርያም ከ ንፋስ ስልክ ሲጫወቱ ተመሳሳይ አደጋዎች አጋጥመው በግል ጥረታቸው ሕይወት ማዳናቸው ይታወሳል።
© ሶከር ኢትዮጵያ