ወልዋሎ ከሦስት ቀናት በኃላ የሚካሄድ ‘እኔ ለወልዋሎ’ በሚል መሪ ቃል የጎዳና ሩጫ አዘጋጅቷል።
በክለቡ ደጋፊ ማኅበር የተዘጋጀው እና በርካታ ደጋፊዎች ይሳተፉበታል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ የጎዳና ሩጫ ገቢው የፋይናንስ አቅም ከማጎልበት አልፎ የደጋፊው አንድነት ለማጠናከር ታስቦ እንደተዘጋጀ ከአዘጋጆቹ ለማወቅ ተችሏል።
ከውድድሩ ከሚገኘው ገቢ ይልቅ በደጋፊው መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር እና ቡድኑ ወደ ዓዲግራት መመለሱን ተከትሎ የመጀመርያ የሜዳውን ጨዋታ ደማቅ ለማድረግ ታስቦ የሚካሄደው ይህ ውድድር ዋና ዓላማው ገቢ ለማግኘት እንዳልሆነ ከውድድሩ አስተባባሪዎች አንዱ የሆነው አቶ ተስፋይ ዮሐንስ ገልፅዋል።
አቶ ተስፋይ ዮሐንስ የውድድሩ ዋና ዓላማ ሲያስረዱም ደጋፊው እንደሁልጊዜው ከክለቡ ጎን እንዲቆም እና ለቡድኑ ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋፅዖ ለማድረግ በአንድነት እንዲቆም የሚያግዝ ውድድር እንደሆነ ይገልፃሉ። “ገቢው እዚ ግባ የሚባል አይደለም፤ የውድድሩ ዋና ዓላማ የደጋፊያችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ቡድናችን ከበርካታ ጊዜያት በኃላ ወደ ዓዲግራት ተመልሶ የሚያደርገው የመጀመርያ ጨዋታን ደማቅ ለማድረግ ነው።” ብለዋል።
አቶ ተስፋይ አክለውም መላው የክለቡ ደጋፊ በእሁዱ የጎዳና ሩጫ እንዲሳተፍ እና ከክለቡ ጎን እንዲቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
©ሶከር ኢትዮጵያ