ድሬዳዋ ከተማ የመስመር ተጫዋች ለማስፈረም ተቃርቧል 

በመቐለ 70 እንደርታ እየተጫወተ የሚገኘው የመስመር ተጫዋቹ እንዳለ ከበደ ቀጣዩ ክለብ ድሬዳዋ ከተማ መሆኑ ዕርግጥ እየሆነ መጥቷል፡፡

በ2010 ክረምት የአርባምንጭ ከተማን ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረድን ተከትሎ በዝውውር መስኮቱ ወቅት ነበር መቐለ 70 እንደርታን የተቀላቀለው የመስመር እና የማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዘንድሮ የመሰለፍ እድል ያላገኘ ሲሆን ከክለቡ ጋር የስድስት ወራት ውል ቢቀረውም በጋራ ስምምነት የሚለያይ ይሆናል። ቀጣይ ማረፊያው ደግሞ ድሬዳዋ ከተማ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ቅድመ ስምምነት የፈፀመው ይህ ተጫዋች የዝውውር መስኮቱ ከቀናት በኃላ ሲከፈት የመጀመሪያው የክለቡ ፈራሚ እንደሚሆን ሲጠበቅ በመስመር ማጥቃት አማራጩ ለጠበበው ድሬዳዋም ችግር ፈቺ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቀጣዮች የዝውውር ቀናት አራት ያህል ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም የሚጠበቀው ድሬዳዋ ከተማ በመስከረም ወር ላይ ለክለቡ ፊርማውን አኑሮ ከነበረው ናይጄሪያዊው አጥቂ ባጅዋ አዴሴጎን ከሰሞኑ እንደሚለያይም ታውቋል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ