ወልዋሎዎች ከተጫዋቾች ጉዳት ፋታ እያገኙ ነው

በጉዳት ሲታመስ የቆየው ወልዋሎ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ከጉዳት መልስ እያገኘ ነው።

በሊጉ መጀመርያ ላይ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈው ለሳምንታት ሊጉን መምራት የቻሉት ወልዋሎዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታቸው አሽቆልቁሎ ቡድኑ ወራጅ ቀጠና ላይ መግባቱ ይታወሳል። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ነገሮች በርካታ ቢሆኑም የተጫዋቾች ጉዳት ጉዳይ ቀላል ድርሻ አልነበረውም።

ባለፉት በርካታ ሳምንታት አምበሉ ዓይናለም ኃይለ፣ ካርሎስ ዳምጠው፣ አቼምፖንግ አሞስ፣ ፍቃዱ ደነቀ፣ ሰመረ ሀፍታይ እና ዓብዱልዓዚዝ ኬይታ (ባለፈው ሳምንት ከጉዳት ተመልሷል) በጉዳት ያጡት ወልዋሎዎች የተወሰኑ ተጫዋቾች ከጉዳት ተመልሰውላቸዋል።

ቡድኑን በቋሚነት ሲያገለግሉ የነበሩት አይናለም ሀይለ ፣ አቼምፖንግ አሞስ እና ፍቃዱ ደነቀ ልምምድ የጀመሩ ሲሆን ለጨዋታ ብቁ ከሆኑም በቀጣይ እሁድ ወልቂጤ ከተማን በሚገጥመው ስብስብ ይካተታሉ ተብሎ ይገመታል። ቀለል ያለ ልምምድ በግሉ የጀመረው ካርሎስ ዳምጠውም የጤንነት ሁኔታው በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ