የእግር ኳስ ህይወቱን በሀዋሳ ከተማ የጀመረውና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታው በርካታ ድሎችን ማጣጣም የቻለው፣ ለብሔራዊ ቡድንም ወሳኝ አግልጋሎት የሰጠው ሁለገቡ እና አንጋፋው ተጫዋች አዳነ ግርማ አሁንም በምርጥ አቋም በአዲስ አዳጊው ክለብ ወልቂጤ ከተማ በተጫዋችነት እና በምክትል አሰልጣኝነት እያገለገለ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመኑ ባየርን ሙኒክ እግር ኳስ ክለብ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የ2ኛ ዙር የጀማሪ እግርኳስ አሰልጣኞች ስልጠናን በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተከታተለ ይገኛል። በርከት ያሉ የቀድሞ ተጫዋቾች እየተከታተሉ በሚገኙበት በዚህ ስልጠና ዙርያ አዳነ ግርማ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ ስለ ስልጠናው ጠቀሜታ የሚከተለውን ብሏል
” ይህ ስልጠና ለሁለተኛ ዙር የተዘጋጀ ነው። ስልጠናው መሠረት ያደረገው ታዳጊዎችን እንዴት ማብቃት እንደሚቻል ትኩረቱን ያደረገ ነው። በመጀመርያው ዙር ከ7–12 ዓመት የሚገኙ ታዳጊዎች ላይ ነው። አሁን እየወሰድን የምንገኘው ደግሞ ከ12–15 ዓመት በሚገኙ ታዳጊዎች ላይ ነው። ባየርሙኒክ የመጡት ባለሙያዎች ታዳጊዎችን ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ እንዴት አድርገን ልምምድ ማሰራት እንዳለብን፣ ቴክኒካል ክህሎታቸውን እንዴት መጨመር እንዳለብን፣ ኳስ በየትኛው እግር መጠቀም እንደሚገባ፣ ኳስ እንዴት እንደሚነጠቅ…ብቻ ሰፊ የሆነ እና የእነርሱን አሰለጣጠን ዘይቤ የምንከታተልበት ትልቅ ስልጠና ነው። በጣም የሚገርመው ለእኛ ጥቃቅን ትንሽ የሚመስለውን ነገር እነርሱ ትኩረት በመስጠት ነው የሚያሰሩት። ጀርመኖች እግርኳሳቸውን ያሳደጉት እና እዚህ ደረጃ የደረሱት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እያሰለጠኑ መሆኑን ተረድቼበታለው። እኛ ሀገርም ታዳጊዎች በዚህ መንገድ ቢሰለጥኑ የማይቀየሩበት ምክንያት የለም።
” ይህ ነገር ትኩረት ተሰጥቶበት በደንብ ከተሰራ እግርኳሱን መታደግ ይችላል። ጀርመኖች ዓለም ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ ወጣቶችን መፍጠር የቻሉት እና እነርሱ በእግርኳሱ ያሉበትን ከፍተኛ ደረጃ የደረሱት እንደዚህ ሰርተው ነው። ስለዚህ ለእኛ ይህ ትልቅ ትምህርት ነው። እኔ በበኩሌ ይህ ስልጠና ለተከታታይ ሁለት ጊዜ ስወስድ የመጀመርያዬ ነው። ትልቅ ትምህርት እያገኘሁበት ነው። ብዙ ልምድ አለኝ፤ በተጫዋችነትም አሳልፌያለው። አሁን ያገኘሁትን ስልጠና ስደምርበት ትልቅ ደረጃ እደርሳለው። ከታች ከማይታወቅ አካባቢ ተነስቼ ፈጣሪ ይመስገን ትልቅ ተጫዋች ሆኛለው። ትልቅ አሰልጣኝ የማልሆንበት ምንም ምክንያትም የለም። ”
© ሶከር ኢትዮጵያ