ከዚህ በፊት በሶከር ሜዲካል አምዳችን የአዕምሮ ጤና በእግር ኳስ ላይ ያለውን አስፈላጊነት ተመልክተናል። በዚህኛው ፅሁፋችን ደግሞ በስፖርቱ ዙርያ ያሉ አካላት ይህንን ወሳኝ ጉዳይ እንዴት ትኩረት በመስጠት ማሳደግ እንዳለባቸው እንመለከታለን።
በሀገራችን በአጠቃላይ ስለ አዕምሮ ጤና ያለን ግንዛቤ አናሳ የሚባል ነው። ስለችግሮቻችን በግልፅ ማውራት እና መፍትሄን ለመፈለግ መጣር እምብዛም የተለመደ አይደለም። ነገር ግን ከአዕምሮ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ዋናው እርምጃ በግልፅ መወያየት መቻል ነው። በተለይም ጭንቀት እና ድባቴን የመሳሰሉ ዕከሎችን ለመቋቋም ከቤተሰብ አባል ሆነ ባለሙያ ጋር የሚደረግ መማከር ያለው ጠቀሜታ ላቅ ያለ ነው።
በምዕራቡ አለም ከላይ ስለተጠቀሱት ችግሮች ማውራት የተለመደ ነው። ታዋቂ ተጫዋቾች ሆኑ አሰልጣኞች ስለጉዳይ በተለያየ ጊዜ መግለጫን ሲሰጡ ማየት አዲስ አይደለም። በቅርቡ በአብዛኛው የእግር ኳስ አፍቃሪ ዘንድ በጉጉት የሚታየው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በኤፍ ኤ ካፕ ጫወታዎች ወቅት ሁሉም ግጥሚያዎች በአንድ ደቂቃ ዘግይተው እንዲጀምሩ በዚህም ሂደት ተመልካቹ ስለአዕምሮ ጤና እንዲያስብ ለማድረግ ተችሏል። ባሳለፍነው ሳምንትም ሁሉም ክለብ በመለያው ላይ “Heads Up” የሚል ፅሁፍን በማስፈር ድጋፋቸውን ገልፀዋል።
የቀድሞው የሊቨርፑል ተጫዋች ጄሰን ማከቲር ስለ አዕምሮ ጤና እንዲህ ብሏል፡-
“ችግሩ ስለአዕምሮ ጤና ካለው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ በግልጽ መናገር የተለመደ አይደለም፡፡ ይህም ማንም ሊረዳን እንደማይችል እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ትክክለኛው እርምጃ ስለጉዳዩ መነጋገር መቻል ነው፡፡ ይህን ሰምቶ የሚረዳን ሰው መኖሩ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡ በበኩሌ ከቤተሰብ እና ከጓደኞች በተጨማሪ ከባለሙያ ጋር መወያየት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሂደቱ ጊዜ የሚፈልግ ነበር፡፡ ከ6 እስከ 7 ወራት ፈጅቶብኛል፡፡ እኔ በታጫወትኩበት ጊዜ እና አሁን ያለው ልዩነት ሰፊ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግንዛቤአችን ላቅ ያለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከአካዳሚ ጀምሮ ባለሙያዎች በቅርበት የሚሰሩ ሲሆን ማንኛውም ተጫዋች እርዳታን ማግኘት ይችላል፡፡ “
የሀገራችን እግርኳስ ማደግ የሚችለው በታክቲካዊ ዕውቀት እና በቴክኒካዊ ብቃት የላቁ ተጫዋቾች ሲኖሩን ብቻ ሳይሆን ጤናቸው ሙሉ መሆን ሲችልም ጭምር ነው፡፡ የአዕምሮ ጤና ደግሞ ለማንኛውም ተጫዋች እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ያለው አስፈላጊነት እንዴት ላቅ ያለ መሆኑን ከላይ በተመለከትናቸው ምሳሌዎች አስተውለናል። ስለዚህም ሚዲያውን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከተው አካል ይህን ጉዳይ በትኩረት ሊወያይበት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽሁፍም ልናሰምርበት የምንወዳቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፡-
– ተጫዋቾች ከአሰልጣኞች እና የህክምና ባለሙያዎች ጋር በግልጽ የሚወያዩበት አጋጣሚ ሊመቻች ይገባል፡፡
– ሁሉም ተጫዋች የሚሰማውን ስሜት በግልጽ ለመናገር ማንገራገር የለባቸውም፡፡
– ፌደሬሽኑም ሆነ የስፖርት እና ወጣቶች ሚኒስቴር የተለያዩ የመወያያ መድረኮችን ማመቻቸት አለበት፡፡
– ክለቦችም ተጫዋቾቻቸው ስለ ጉዳዩ ያላቸውን ግንዛቤ ማየት እና የሚያስፈልገውን እርዳታ ሊያደርግ ያስፈልጋል፡፡
– ሚዲያውም ውጤቶች እና ሜዳ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሳዎችን ብቻ ሳይሆን ይህም የጤና ጉዳይ ይመለከተኛል ብሎ መስራት ይኖርበታል፡፡
©ሶከር ኢትዮጵያ