ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ጅማ አባ ጅፋር

በ15ኛ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ ግብር ሀዋሳ ላይ የሚደረገውን የሀዲያ ሆሳዕና እና ጅማ አባ ጅፋር የነገ 9:00 ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ባለፈው ሳምንት በአዲስ አሰልጣኝ ስር የመጀመርያ ነጥባቸው ያሳኩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ተስፋቸውን ለማለምለም በዚህ ጨዋታ ሶስት ነጥብ ማሳካት ብቸኛው አማራጫቸው ነው።

የሀዲያ ሆሳዕና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ ተሸነፈ

ባለፉት ጨዋታዎች በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የነበራቸው ነብሮቹ በነገው ዕለት ከአጨዋወታቸው ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል እና ጥንቃቄን የሚያስቀድም ቡድን እንደመግጠማቸው ካለፉት ጨዋታዎች ለየት ያለ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ባለፉት ጨዋታዎች በቡድኑ አጨዋወት ላይ እንደሚፈለገው ድርሻ ያልነበራቸው ሶስቱ ጥሩ አማካዮች በዚ ጨዋታ ወሳኝ ሚና ይዘው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁን እንደሻው፣ አፈወርቅ ኃይሉ እና በኃይሉ ተሻገር የመሳሰሉ ለኳስ ቁጥጥር አመቺ የሆኑ አማካዮች የያዘው የሀዲያ ሆሳዕና የአማካይ ክፍል ምንም እንኳ ባለፉት ጨዋታዎች ጥንቃቄን መርጦ በመጫወቱ የተጫዋቾቹን አቅም አሟጦ ባይጠቀምም በዚ ጨዋታ ግን የተጋጣሚው ጠጣር አቀራረብ የተጠቀሰው አጨዋወት እንዲከተል ያስገድደዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በነብሮቹ በኩል ደስታ ጊቻሞ በጉዳት የማይሰለፍ ሲሆን አብዱልሰመድ ዓሊ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ቡድኑ ተመልሷል፡፡

የጅማ አባ ጅፋር ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ አቻ አቻ

ባለፈው ሳምንት በሜዳቸው ድሬዳዋን የረቱት ጅማ አባ ጅፋሮች በጥሩ መነቃቃት ተከታታይ ድላቸውን አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ።

ቡድኑ በሜዳ ላይ ውጤቱ ወጣ ገባ ከመሆኑ ባሻገር ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ያለው ችግር በመጠኑም ቢሆን መቀረፉ ተጫዋቾቹ በጥሩ ተነሳሽነት እንዲያደርጉ እንደሚረዳቸው ይጠበቃል። በተጨማሪም አሰልጣኙን መልሶ ማግኘቱ፣ ጨዋታው በገለልተኛ ሜዳ መከናወኑ እና ተጋጣሚው የማሸነፍ ጫና ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን እንደሚከውን መጠበቁ ለጅማ ግምት እንዲሰጥ ያደርገዋል።

ቡድኑ በአጨዋወት ረገድ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾቹን ከኳስ ጀርባ በማድረግ በመልሶ ማጥቃት የጎል እድሎችን የሚፈጥር ቡድን እንደመሆኑ በነገው ጨዋታም ይህንኑ አቀራረብ ምርጫው እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ሰሞኑን ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ልምምድ በበቂ ሁኔታ አለመስራታቸውና ሀዋሳ የሚገቡት ነገ ከመሆኑ ጋር ተደማምሮም መከላከልን የመጀመርያ ምርጫ አድርገው እንደሚገቡ ይገመታል።

ጅማ አምረላ ደልታታን በጉዳት አብርሀም ታምራት እና አሌክስ አሙዙን በቅጣት እንዲሁም ከቡድኑ ጋር የተለያየው ብሩክ ገብረአብን የማይጠቀም ሲሆን ከግል ጉዳዩ የተመለሰው ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙም መሰለፉ አጠራጥሯል፡፡

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (4-4-2)

አቬር ኦቮኖ

ፀጋሰው ዴማሞ – በረከት ወልደዮሐንስ – አዩብ በቀታ – ሄኖክ አርፊጮ

በኃይሉ ተሻገር – ይሁን እንዳሻው – አፈወርቅ ኃይሉ – ሱራፌል ዳንኤል

ቢስማርክ አፒያ – ቢስማርክ ኦፖንግ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

መሐመድ ሙንታሪ

ጀሚል ያዕቆብ – ከድር ኸይረዲን – መላኩ ወልዴ – ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገ/ሥላሴ – ሄኖክ ገምቴሳ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ኤልያስ አህመድ – ተመስገን ደረሰ

ብዙዓየው እንዳሻው

© ሶከር ኢትዮጵያ