በጉዳት እየታመሱ የሚገኙት የጣናው ሞገዶች 5 ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን ከጉዳት መልስ አግኝተዋል።
ከጉዳታቸው ያገገሙት ተጨዋቾች አዳማ ሲሶኮ፣ ሳላምላክ ተገኝ፣ ፍፁም ዓለሙ፣ ዜናው ፈረደ እና ማማዱ ሲዲቤ ናቸው። ከጅማ አባጅፋር ቡድኑን ዘንድሮ የተቀላቀሉት ሁለቱ ግዙፍ ተጨዋቾች አዳማ ሲሶኮ እና ማማዱ ሲዲቤ በተመሳሳይ ጉልበታቸው ላይ ካጋጠማቸው ጉዳት በማገገም ልምምድ መስራት ጀምረዋል። በተለይ የተከላካይ መስመር ተጨዋቹ ሲሶኮ ካጋጠመው ጉዳት በጥሩ ሁኔታ በማገገሙ ሙሉ የልምምድ ጊዜያትን ከቡድን አጋሮቹ በመሆን መስራቱ ተነግሯል። ነገር ግን 5 ጎሎችን ለቡድኑ ያስቆጠረው ማማዱ ሲዲቤ መጠነኛ ስሜቶች አሁንም እየተሰማው በመሆኑ ልምምዶችን በከፊል ብቻ እያከናወነ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በዘንድሮ የውድድር ዓመት በመስመር ተከላካይ ቦታ ጥሩ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘው ሳላምላክ ተገኝ ከጉዳቱ ያገገመ ሌላኛው ተጨዋች ነው። ጥርሱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ለቡድኑ ግልጋሎት እየሰጠ የማይገኘው ይህ ተጨዋች ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ በማገገሙ በሳምንቱ መጀመሪያ ወደ ስብስቡ ተቀላቅሎ ልምምዱን አከናውኗል።
ከሶስቱ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች በተጨማሪ ከአንድ ጨዋታ በፊት(ከሰበታ ከተማ ጋር) ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ፍፁም ዓለሙ በተመሳሳይ ከጉዳቱ ማገገሙ ተነግሯል። ከዚህ ውጪ በመስመር አጥቂነት የሚጫወተው ዜናው ፈረደ ዛሬ ረፋድ ካጋጠመው የእግር ጉዳት መልስ ልምምድ አከናውኗል። ይህንን ተከትሎ ምናልባት አምስቱ የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች (የሲዲቤ አጠራጣሪ ቢሆንም) በእሁዱ የስሑል ሽረ ጨዋታ እንደሚደርሱ ተጠቁሟል።
ባህር ዳር ከተማ እነዚህን 5 ተጨዋቾች ከጉዳት መልስ ለጨዋታ ቢያገኝም አምበሉን ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ወሰኑ ዓሊን በመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታ እንደማይጠቀም ተነግሯል።
© ሶከር ኢትዮጵያ