ሀዋሳ ላይ የሚደረገውን የሲዳማ ቡና እና የሰበታ ከተማን ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ከሁለት ጨዋታዎች በፊት(ጥር 24) በቅዱስ ጊዮርጊስ የደረሰባቸው አሰቃቂ ሽንፈት ያነቃቸው ሲዳማ ቡናዎች በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ያገኙትን ድል ለመድገም እና የሊጉን የመጀመሪያ ዙር በመልካም ውጤት ለመቋጨት ነገን ይጠባበቃሉ።
የሲዳማ ቡና ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ |
በሊጉ ብቸኛው አቻ ያልወጣ ክለብ የሆነው ሲዳማ ቡና በወጣ ገባ አቋሙ ዓመቱን ለማጋመስ ነገ ወደ ሜዳ ይገባል። እርግጥ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድኑ የተሻሉ ነገሮችን ቢያስመለክትም ፍሬያማ የመሆን ችግር ተጠናውቶታል።
ቡድኑ በ14ቱ የሊጉ ጨዋታዎች የመስመር ላይ አጨዋወትን በፍጥነት በማከናወን ሲንቀሳቀስ ታይቷል። በተለይ ደግሞ ሃዋሳ ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎችን ውጤት በመስመር ተጨዋቾቹ ፍጥነት ለመወሰን በመጣር ይንቀሳቀሳል። ነገም ቡድኑ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት በመጠቀም እና የሰበታን የተከላካይ መስመር በመዘርዘር ክፍተቶችን ለመፈለግ እንደሚጥር ይገመታል። ለዚህ አጨዋወቱ ደግሞ ፈጣኖቹ የቡድኑ አጥቂዎች አዲስ እና ሀብታሙ ከዮሴፍ እና አበባየሁ የሚላክላቸውን የአግድሞሽ ኳሶች በመጠቀም ግቦችን ለማስቆጠር እንደሚታትሩ ይታሰባል። ከሁለቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ ይገዙ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ያለው ብቃት የተሻለ በመሆኑ ለቡድኑ ሌላ አማራጭ ሊሰጥ ይችላል።
በአብዛኞቹ የሜዳው ላይ ጨዋታዎች አጥቅቶ ለመጫወት የማይቦዝነው ቡድኑ ያለው የመከላከል አደረጃጀት ልፋቱን መና እያስቀረበት ይገኛል። በተለይ ደግሞ የተረጋጋ ጥምረት በየጨዋታዎቹ እያስመለከተ የማይገኘው የቡድኑ የተከላካይ መስመር በሽግግሮች ወቅት እጁን በቀላሉ ለተጋጣሚ ሲሰጥ ይታያል። ነገም ምናልባት ተጋባዦቹ ሰበታዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚያልሙ ከሆነ ይህ ፍጥነት አልባው የቡድኑ የኋላ መስመር ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል።
በቡድኑ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና እንደሌለ ተነግሯል። ይልቁንም ዳዊት ተፈራ፣ ጊት ጋትኮች እና ዮናታን ፍሰሃ ካጋጠማቸው ጉዳት በማገገማቸው ለነገው ጨዋታ ብቁ እንደሆነ ተጠቁሟል።
የሰበታ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
አቻ | ተሸነፈ | አሸነፈ | ተሸነፈ | አሸነፈ |
በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ሰበታ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመራቅ እና ዓመቱን በድል ለማጠናቀቅ ሃዋሳ ገብተዋል።
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ቡድኑ እንደ ሌሎቹ የሊጉ ክለቦች ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጪ ማሸነፍ ይቸግረዋል። በተለይ ደግሞ ፍጥነት ያላቸው የአጥቂ መስመር ተጨዋቾችን የያዘ ተጋጣሚ በሚያገኝበት ወቅት ቡድኑ በቀላሉ ይፈተናል።
በተደጋጋሚ ኳስ ከግብ ጠባቂ መስርቶ ለመወጣት የሚሞክረው ቡድኑ በነገው ጨዋታ አቀራረቡን በመለወጥ ለጨዋታው እንደሚቀርብ ይገመታል። በተለይ ደግሞ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ መጫወቱ እንዲሁም የተጋጣሚ አጥቂዎች እና አማካዮች ታታሪነት ቡድኑን እንደ ኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ እንዲጫወት እንደሚያደርገው ይታሰባል። በዚህም ቡድኑ ረጃጅም ኳሶችን 6 ጎሎች ላስቆጠረላቸው ፍፁም በመላክ እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቶችን በመስመር በኩል በመተግበር ግቦችን ለማስቆጠር ይጥራል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ የቡድኑን የአማካይ መስመር እና የአጥቂ መስመር በጥሩ ሁኔታ ለማገናኘት የሚጥረው ታደለ በነገውም ጨዋታ ልዩነት ፈጣሪ ሊሆን ይችላል። ታደለ ከአጠገቡ ካሉት የአማካይ ተጨዋቾች ጋር ካለው ጥሩ መናበብ በተጨማሪ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን የሚያስጀምርበት መንገድ እና ከተከላካይ ጀርባ የሚልካቸው ኳሶች ሲዳማዎችን ሊረብሽ ይችላል።
በቅርብ ጊዜያት የቀኝ መስመር ቦታ ላይ ለውጥ እያደረጉ የመጡት ሰበታዎች ነገ በዚህ መስመር እንዳይቸገሩ አስግቷል። በተለይ በዚህ ቦታ እየተሰለፈ የሚገኘው ኢብራሂም ካለበት የቦታ አጠባበቅ ስህተት እና የመከላከል አቅም ማነስ አንፃር ቡድኑ ሊቸገር ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ሲዳማዎች በመስመር ላይ አጨዋወት የተካኑ መሆናቸው ጉዳዩን ያገስፈዋል። ከዚህ ውጪ በሁለቱ የቡድኑ የመሃል ተከላካዮች መካከል እየተፈጠረ ያለው ሰፊ ርቀት የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ(ሲዳማ) ተጠቃሚ እንዳያደርግ አሳስቧል።
እንደ ባለሜዳዎቹ ሁሉ ሰበታዎችም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለባቸውም። ነገር ግን ምክንያቱ ባልታወቀ ጉዳይ የቡድኑ አምበል መሱዑድ መሃመድ፣ በሀይሉ አሰፋ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከቡድኑ ጋር ወደ ሃዋሳ እንዳላመሩ ለማወቅ ተችሏል። በአንፃሩ ጉዳት ላይ የሰነበተው የቡድኑ የመስመር አጥቂ አሰቻለው ግርማ ከጉዳቱ መመለሱ ተነግሯል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሲዳማ ቡና (4-3-3)
ፍቅሩ ወዴሳ
አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ክፍሌ ኪአ – ግሩም አሰፋ
ብርሀኑ አሻሞ – ዮሴፍ ዮሐንስ – አበባየው ዮሐንስ
አዲስ ግደይ – ይገዙ ቦጋለ – ሀብታሙ ገዛኸኝ
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል አጃይ
ኢብራሂም ከድር – አዲስ ተስፋዬ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃ/ሚካኤል አደፍርስ
ደሳለኝ ደባሽ – አቤል ታሪኩ – ታደለ መንገሻ
አስቻለው ግርማ – ፍፁም ገ/ማርያም – ባኑ ዲያዋራ
© ሶከር ኢትዮጵያ