ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእግርኳስ ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጣሊያኑ ኤሲ ሚላን ደብዳቤ እንደደረሰው ሰምተናል።
ከሞሮኮ እና ከብራዚል እግርኳስ ፌዴሬሽኖች እንዲሁም ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ ክለብ ጋር ትብብር በማድረግ በእግርኳስ ልማት ላይ በማተኮር የአሰልጣኞች ስልጠና እያዘጋጀ የሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሁን ደግሞ ከአንጋፋው የጣልያን እግርኳስ ክለብ ኤሲ ሚላን ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለው ደብዳቤ እንደደረሰው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ተናግረዋል።
ዛሬ በተጠናቀቀውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የ2ኛ ዙር የጀማሪ እግርኳስ አሰልጣኞች ስልጠና መዝጊያ ላይ “እግርኳሱን ለማዘመን ከባየር ሙኒክ ጋር የጀመርነውን የትብብር ስራ እየቀጠልን ነው። ኤሲ ሚላንም ደብዳቤ ልኮልናል።” በማለት ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ ይሄን ይበሉ እንጂ ዝርዝር መረጃዎችን አልተናገሩም። ምን አልባትም ከባየር ሙኒክ ጋር በጋራ ለመስራት ከተደረገው ስምምነት ጋር ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የሚኖሩ መረጃዎችን በቀጣይ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ