ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳካ

በአስራ አምስተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ሀዲያ ሆሳዕና በአዩብ በቀታ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ጅማ አባ ጅፋርን 1ለ0 ረቷል፡፡

ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ መቐለ አምርተው ከስሑል ሽረ ያለ ግብ ባጠናቀቁበት ጨዋታ የተጠቀሙበትን ስብስብ ዛሬም ይዘው ወደ ሜዳ ሲገቡ ጅማ አባ ጅፋሮች ድሬዳዋን በሜዳቸው ሲረቱ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ውስጥ በቅጣት በሌለው አሌክስ አሙዙ ምትክ ከድር ኸይረዲንን ብቻ ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ከጨዋታው እንቅስቃሴ ይልቅ የጅማ ተጫዋቾች እለቱ ዳኛ ጋር የሚፈጥሩት ሰጣ ገባ እንዲሁም ረጃጅም እና የሚቆራረጡ ቅብብሎች በዝተው የታዩበት ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የቀይ መስቀል አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች በሜዳ ላይ እስከ ሁለተኛው አጋማሽ መባቻ ድረስ ያላየንበት ሌላኛው የጨዋታው ክስተት ነበር፡፡

ሀዲያ ሆሳናዎች ከአማካያቸው አፈወርቅ ኃይሉ ከሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ወደ ቀኝ በኩል አዘንብለው በቢስማርክ አፒያ መጫወትን የመረጡበት፤ ለዚህ ጨዋታ ዛሬ ረፋድ 4:30 ሀዋሳ የደረሱት ጅማ አባ ጅፋሮችም በተመሳሳይ እንደ ነብሮቹ ሁሉ ረጃጅም የሆኑ እና ለአጥቂው ብዙዓየው እንዳሻው በሚጣሉ ኳሶች ወደ ፊት ሰብረው ለመግባት ጥረት ማድረግ የቻሉበት ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሁለቱም ቡድኖች የኳሱ ማረፊያ ብኩኖች ነበሩ፡፡

ሱራፌል ዳንኤል ባደረጋት የርቀት ሙከራ በተወሰነ መልኩ ወደ ሳጥን መጠጋት የጀመሩት ሆሳዕናዎች ብልጭ ብለው በማጥቃቱ ኃላ ላይ ጥፍት ቢሉም ያገኟቸውን መልካም አጋጣሚዎች በግድየለሽነት አምክነዋል፡፡ በተለይ ቢስማርክ አፒያ በተደጋጋሚ የሚያገኛቸውን ኳሶች ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ እየሆነ በእለቱ ዳኛ ሲነፋበት ያየንበት ሌላኛው አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡ 32ኛው ደቂቃ ላይ የእለቱ የጨዋታውን ኮሚሽነር ግዛቴ አለሙ ከትሪቡን ወርደው ወደ ሜዳው በመግባት የጅማ አባ ጅፋሩ የመሀል ተከላካይ ከድር ኸይረዲን ያደረገው ካሶቶኒ (ካልኪ) ከቡድኑ ተጫዋቾች ጋር የማይመሳሰል በመሆኑ እንዲለውጥ ያስደረጉ ሲሆን ሜዳ ላይ የተለመዱት የቀይ መስቀል ባለሙያዎች ሜዳ ውስጥ ባለመኖራቸው በፍጥነት እንዲመጡም ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ይህም ዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢዎች ከጨዋታው በፊት ማድረግ የነበረባቸውን ስራ በአግባቡ ያልሰሩ መሆናቸውን ያሳየን አስገራሚ ክስተትም ነበር፡፡

ከማጥቃቱ በተወሰነ መልኩ ተቆጥበው የዋሉት አባ ጅፋሮች መሀል ላይ ኳስን ይዘው ከመቆየት ባለፈ ወደ ፊት ለማለፍ ተቸግረዋል፡፡ 38ኛው ደቂቃ ላይ በተጨማሪነት ደግሞ የክለቡ ተጫዋቾች ከዳኛው ጋር የፈጠሩት ሰጣገባ እና ውክቢያ ሌላኛው ትኩረት የሚስብ ነበር፡፡ በግራ የአባ ጅፋር የግብ ክልል መላኩ ወልዴ በቢስማርክ አፒያ ላይ ጥፋት ፈፅመሀል በማለት የእለቱ ዳኛ እያሱ ፈንቴ የቅጣት ምት በሚሰጡበት ወቅተ የአባ ጅፋር ተጫዋቾችም ተገቢ ያልሆነ ቅጣት ምት ተሰጥቶብናል በማለት የእለቱን ዳኛ ሲከቡ እና ሲያዋክቡ የታዩ ሲሆን በዚህ መሀል መላኩ ወልዴ፣ ኤልያስ አህመድ እና ኤልያስ አታሮ የቢጫ ካርድን ተመልክተዋል፡፡ ጅማዎችም ዳኛው እየበደለን ነው ሲሉም ክስ በአምበላቸው አማካኝነት ያስያዙ ሲሆን በነኚህ ክስተቶች ጨዋታው አራት ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ሆኗል፡፡

ጨዋታው በዚህች ቅጣት ምት አማካኝነት ወደ ጨዋታ ሲመለስ ተከላካዩ እዮብ በቀታ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ለውጦ ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ ግቧን ካስቆጠረ በኃላ ደስታውን በእንባ ገልጿል፡፡

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ጅማዎች በመልሶ ማጥቃት በኤልያስ አህመድ አማካኝነት መልካም አጋጣሚ ቢያገኙም ግብ ጠባቂው ኦቬር ኦቮኖ አድኖበታል፡፡

የጅማ አባ ጅፋር የማጥቃት እንቅስቃሴ ሚዛን ደፍቶ በታየበት እና የሀዲያ ሆሳዕና አስጠብቆ የመውጣት ፍልሚያ በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ከተሻጋሪ እና ከሁለቱም መስመሮች በሚገኙ መነሾ ኳሶች ሀድያዎችን ሲፈትኑ የዋሉበት ነበር፡፡ በተለይ በቀኝ በኩል ጀሚል ያዕቆብ ሰብሮ ለመግባት ሲያደርግ የነበረው ጥረት አስገራሚ ነበር። ከቅጣት ምት ሄኖክ ገምቴሳ ሲያሻማ መላኩ ወልዴ በግንባር ገጭቶ ለጥቂት በወጣችበት አጋጣሚ ወደ ሆሳዕና ግብ ክልል ማነፍነፍ የጀመሩት አባ ጅፋሮች ያለቀላቸውን ዕድሎች እያገኙ በቀላሉ ስተዋቸዋል፡፡

ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ከርቀት በብዙዓየው እንዳሻው እየመቱ በግብ ጠባቂው አቬር ኦቮኖ ግብ ከመሆን ሲዳንባቸው የዋሉት ጅማዎች ዕድለኛ አልሆኑም እንጂ አስቆጪ ኳሶችን አግኝተው መጠቀም አልቻሉም፡፡ ከተደጋጋሚ ጫና ማሳደር በኃላ በተለይ 83ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንዳሻው ከርቀት አክርሮ መቶ ያኩቡ መሀመድ ጨርፏት ግብ ጠባቂው አቬር ኦቮኖ በግሩም ሁኔታ የያዛት እና 86ኛው ደቂቃ መላኩ ወልዴ ከራሱ ግብ ክልል እየገፋ ወደ ሳጥን ተጠግቶ መቶ ግብ ጠባቂው አቬር ኦቮኖ ሲተፋው ብዙአየው ደርሶ መቶ የግቡ ቀኝ ቋሚ ብረት የመለሰበት ጅማ አባ ጅፋርን አንድ ነጥብ ልታስገኝ የተቃረበች ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተጋጣሚያቸው ለመበለጥ የተገደዱት ሆሳዕናዎች አስጠብቆ ለመውጣት በሚደረግ ትንቅንቅ በመከላከል እና ሰዓት በማዘግየት ሶስት ነጥቧን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ጨዋታውን 1-0 አሸንፈዋል፡፡ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የመጀመሪያ ድላቸው እንደመሆኑ የደስታ አገላለፃቸው ትኩረት ሳቢ ነበር፡፡ ሀዲያ ሆሳዕናም ለመጨረሻ ጊዜ ወልዋሎን ከሜዳው ውጪ 1ለ0 ከረታ በኋላ (ከስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ) ሙሉ ሦስት ነጥብ ያገኘ ሲሆን ይህ የዓመቱ ሦስተኛ ድሉም ሆኖለታል፡፡

በዚህ ጨዋታ አሁንም ሊፈታ ያልቻለው የኳስ አቀባዮች ክፍተት ዛሬም የታየ ሲሆን ኳስን ለመስጠት ሲያዘገዩ በመታየቱም በጅማ አባ ጅፋር የቡድን አባላት ቅሬታ ሲቀርብ በተደጋጋሚ በጨዋታው አይተናል፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ