የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-0 ጅማ አባ ጅፋር

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ በሆነው እና ሀዲያ ሆሳዕና የቅጣቱ የመጨረሻ ጨዋታውን ሀዋሳ ላይ አድርጎ ጅማ አባ ጅፋርን 1ለ0 ከረታ በኋላ የሁለቱ ቡድን ዋና አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተውናል።


“ካጠገባችን ካሉ ክለቦች እንዳንርቅ ነጥቡ አስፈላጊ ስለነበር ተባብረን በጋራ አሳክተነዋል” ፀጋዬ ኪ/ማርያም (ሀዲያ ሆሳዕና)

ስለ መጀመሪያ ድል እና ጨዋታው

ቡድኑን የተረከብኩት አንደኛው ዙር ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታ ሲቀረው ነው፡፡ በመጀመሪያ ከወላይታ ድቻ ጋር ያደረግነው ጨዋታ በሜዳ ላይ ያደረግነው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። ወደ ጎልም ብዙ ደርሰናል። ግን ጫና በተጫዋቾች ላይ ስለነበርን አጨራረስ ላይ ችግር ነበረብን። ከዛ ውጪ ከሜዳችን ውጪ ወደ መቐለ ሄደን የታክቲክ ስራ ሰርተን የቡድኑን መንፈስም መመለስ ስለነበረብን ሶስት ነጥብ እንዳናባክን በጥንቃቄ ተጫውተን አንድ ነጥብ ይዘን መጥተናል። ሶስተኛ ጨዋታችንን ግን ሀዋሳ ማለት ሁለተኛ ሜዳችን ነው፡፡ ደጋፊው ከሆሳዕና የመጣ ብቻ ሳይሆን ሀዋሳ ያለ ከጎናችን እንደሚሆን እናውቃለን። እና የዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ ስለሆነ አጥቅተን መጫወት አለብን። እንደ ጥሎ ማለፍ ባህሪ መጫወት አለብን ብለን ወደ ሜዳ መግባት ነበረብን። ተጫዋቾቻችን እንዳያችሁት ብዙ ጉጉት አለ፤ ጫና አለ። አንደኛውን ዙር ላለመሸነፍ በሚል ትኩረት ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ አድርገን አሸነፈን ወጥተናል፡፡ ከምንም የበለጠ ሦስት ነጥብ ማግኘታችን ነው። በሁሉም ነገር ቡድኑ ሙሉ ነው ባንልም ከውጤት አንፃር አስፈላጊ እና ወሳኝ ነጥብ ስላገኘን። ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ያደረጉት ተጋድሎ የደጋፊዎቻችን ድጋፍ ከአጠገባችን ካሉ ክለቦች እንዳንርቅ ነጥቡ አስፈላጊ ስለነበር ተባብረን በጋራ አሳክተነዋል፡፡ የአንደኛ ዙር ክፍተቶቻችንን አይተን በክለቡ ጥራት እና በተጫዋቾች አጠቃቀም ላይ እንሰራለን። ከዛ ውጪ ደግሞ አንድ ወር የዝግጅት ጊዜ ስለሚኖረኝ ጥሩ ነገር አገኛለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ስለመረጡት መከላከል

ለልጆቹ አንድ ለዜሮውን እርሱት ነው ያልኩት። ጨዋታው የሚቀረው አርባ አምስት ደቂቃ ነው፡፡ ፈሪ ሆናችሁ አትግቡ ባዶ ለባዶ መሆናችሁ አውቃችሁ ግቡ ተጭናችሁ ተጫወቱ ነበር ያልኩት። አንድ ጎል አስተማማኝ አይደለም። ካሉበት ጫና አንፃር ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ከገባ በኋላ ሰባአምስት ፐርሰንቱ የራሳቸው ስለሆነ በተለይ ተከላካዮቹ በቅርበት ለመከላከል ከእኔ ርቀው ስለነበር ተከላካዮች ከግብ ጠባቂው ጋር ተለጥፎ የመጫወት ነገርን ታያለህ። የመጨረሻ አስር ደቂቃ በትክክልም አሰላለፋችንን ለውጠን አስጠብቀን መውጣት ችለናል፡፡ ውጤቱን አስጠብቆ መሄድ በራሱ ስሌት ነው፡፡ ይህ ግን ከዚህ ጫና ለመውጣት የተጠቀምነው ታክቲክ ነው፡፡

ስለመውረድ

ማን እንደሚወርድ እና ማን ሻምፒዮን እንደሚሆን አይታወቅም። የአንደኛ ዙር ጨዋታን ጨርሰናል። ሁለተኛ ዙር የሚመራውም ታች ያለውም ቡድኑን አጠናክሮ ነው ሚመጣው ትልቁ ነገር በክፍተቶቻችን ላይ መስራቱ ነው፡፡ የእኛ መምጣት ቡድኑን በፕሪምየር ሊጉ ማቆየት ነው፡፡ በተቻለኝ መጠን ከተጫዋቾቹ ከደጋውም ጋር ሆኜ ቡድኑን ለማዳን ነው፡፡ እኔ ብቻዬን የትም ልደርስ አልችልም ደጋፊዎችም ከጎኔ ናቸው አመራሩም ተጫዋቹም ከጎኔ ናቸው። በጥራት ዙርያ አስተካክለን ተጫዋች ካገኘን አምጥተን በፕሪምየር ሊጉ ለመቆየት ነው እቅዳችን ፡፡ አሁን ግን ወራጅ አይለይም። ምክንያቱም አንድ ስታሸንፍ ከላይ ትመጣለህ፡፡

“ከእረፍት በኋላ ሙሉ በሙሉ አጥቅተን ነበር የተጫወትነው” ጳውሎስ ጌታቸው (ጅማ አባ ጅፋር)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታውን እንደተመለከታችሁት ነው እንዲህ አይነት ክስተት ይፈጠራል። በተለይ ከእረፍት በኋላ በሙሉ አጥቅተን ነበር የተጫወትነው። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች መጠቀም አልቻልንም። ጥሩ ጨዋታ ነው፤ በኔ አመለካከት መጥፎ ጨዋታ አይደለም። ቡድናችን አንደኛ ልምምድ ሳይሰራ የመጣ ቡድን ነው። ብዙ ነገሮችን አርመን አይደለም የመጣነው። ከድሬዳዋ ጨዋታ በኋላ ቀላል ልምምድ ሰርተን ነው የመጣነው በአጠቃላይ እንደኔ እይታ ጥሩ ነው፡፡

የደመወዝ ክፍያው በቡድኑ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ

ለኔ እንደዚህ አይነት ነገር ባትጠይቁኝ ደስ ይለኛል። አንደኛ የኔ ስራ ማሰልጠን ነው፡፡ ስራዬ እዚህ ጋር ያገኘኋቸውን ልጆች ጥሩ ነገር ላይ ማብቃት ነው፡፡ ቡድኑ አጥቅቶ መጫወት ይችላል። ሁሉንም ነገር አድርጎ የተጫወተ ቡድን ነው። ይህን ጥያቄ ለአስተዳደር ሰዎች ብጠይቁ ይሻላል። እኔ መናገር አልፈልግም፡፡

በጫና ውስጥ ሆኖ ጥሩ የመንቀሳቀስ ምስጢር

እኔ እና ተጫዋቾቼ መሀል ማንም ሰው አይገባም። ሌላው ነገር እንዳለ ሆኖ ስራችን ላይ እንከባበራለን። በአጠቃላይ ቡድኑ ኳስ ነው የሚጫወተው። ሌላ ነገር የለውም። የተሟላለት ቡድን ነው የሚመስለው። ሁለተኛ ዙር ላይ ይሄን አስቀጥዬ መሄድ ነው ምፈልገው፡፡

© ሶከር ኢትዮጵያ