ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ስሑል ሽረ

የጣና ሞገዶቹ ስሑል ሽረን የሚያስተናግዱበት የ15ኛ ሳምንት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

በሜዳቸው ድንቅ የማሸነፍ ክብረ ወሰን ያላቸው ባህርዳር ከተማዎች በመጨረሻው የዙሩ ጨዋታ ላይ አሸንፈው ወደ መሪዎቹ ለመጠጋር አልመው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።

የባህር ዳር ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ከሜዳቸው ውጭ ጠጣር አቀራረብ ይዘው የሚቀርቡት ስሑል ሽረዎችን የሚገጥሙት ባህር ዳር ከተማዎች በነገውም ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንደሚኖራቸው ይታሰባል። በተለይም ቡድኑ በሜዳው መጫወቱ እና የተጋጣሚው ቡድን ለኳስ ቁጥጥር ያለው አነስተኛ ፍላጎት ቡድኑን የኳስ ቁጥጥር የበላይነትነት እንዲኖረው ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

ቡድኑ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ የሜዳው ላይ ጨዋታዎቹ የግራ መስመሩን በደንብ ይጠቀማል ተብሎ ሲገመት በዚህ መስመር ላይ የተሰለፈው ፈጣኑ ግርማ ዲሳሳም በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል። ሆኖም ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር የሚቸገረው ቡድኑ የነገው ተጋጣሚው ስል የመልሶ ማጥቃት ቡድን እንደመሆኑ በነገው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃት እንዳይፈተን ያሰጋል። በዚህም ቡድኑ የመስመር ተከላካዮቹን እንቅስቃሴ ይገድባል ተብሎ ሲጠበቅ ለተጋጣሚ የመልሶ ማጥቃትም ልዩ ዝግጅት ማድረጉ አይቀሬ ነው።

ባህር ዳር ከተማዎች በጉዳት ላይ የሰነበቱ ተጨዋቾቻቸው ማግኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። በተለይም የፍፁም እና የሲሶኮ ወደ ጨዋታ መመለስ የቡድኑን የፊት እና የኋላ መስመር የሚያጠናክር ይሆናል።

የጣና ሞገዶቹ በነገው ጨዋታ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ወሰኑ ዓሊን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም በአንፃሩ አዳም ሲሴኮ ፣ ፍፁም ዓለሙ እና ሳላአምላክ ተገኘ ከጉዳት መልስ ቡድናቸው ያገለግላሉ። ሆኖም ቀለል ያለ ልምምድ የጀመሩት ዜናው ፈረደ እና ማማዱ ሲዲቤ የመሰለፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።

የስሑል ሽረ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አቻ አሸነፈ ተሸነፈ አቻ

በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ጥለው ወደ ሊጉ አናት የሚጠጉበትን ዕድል ያባከኑት ስሑል ሽረዎች የዙሩ አጨራረሳቸውን ለማሳመር እና ከመሪዎቹ ላለማራቅ ከነገው ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት የግድ ይላቸዋል።
ከሜዳቸው ውጭ ባድረጓቸው አብዛኞቹ ጨዋታዎች ጥንቄቃን መርጠው የገቡት ሽረዎች በነገው ጨዋታም ጠጣር እና ለተጋጣሚ ክፍተት የማይሰጥ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ሲጠበቅ የተጋጣምያቸው ክፍት አጨዋወትም ከባለፉት የሜዳ ውጭ ጨዋታዎች በተሻለ ድፍረት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ለመተግበር ምክንያት ይሆናቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ጠጣር አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብለው የሚገመቱት ሽረዎች በአማካይ ጥምረታቸው ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ሲጠበቅ አጨዋወቱን በተሻለ መንገድ ለመተግበር የሚመቸው አክሊሉ ዋለልኝ ከረጅም ግዜ በኃላ ወደ ቋሚነት ይመለሳል ተብሎ ይገመታል።

የመልሶ ማጥቃት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግራቸው በተጋጣሚዎች ተገማች እያደረጋቸው የሚገኙት ሽረዎች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥማቸው ይሰጋል። አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ እና ረዳቶቹም ለዚህ መፍትሄ የሚሆን ተለዋጭ አቀራረብ የማዘጋጀት ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በቆመ ኳስ አጠቃቀም ጥሩ ክብረ ወሰን ያለው ቡድን እንደመግጠሙ ለተጠቀሰው የተጋጣሚ ጠንካራ ጎን የተለየ ዝግጅት ማድረጉ አይቀሬ ነው።

ስሑል ሽረዎች በነገው ጨዋታ ዲዲዬ ለብሪ እና ወንድወሰን አሸናፊ በቅጣት ሀይልአብ ኃይለሥላሴ እና ዮናስ ግርማይ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። ባለፈው ሳምንት አንገቱ ላይ ቀላል ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ምንተስኖት አሎ የቀድሞ ክለቡን ለመግጠም በጥሩ ጤንነት ሲገኝ በአምስት ቢጫ ጨዋታ ያለፈው አዳም ማሳላቺም ቅጣቱን ጨርሶ ወደ ባህር ዳር አቅንቷል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ዐምና ተያይዘው ወደ ፕሪምየር ሊግ የመጡት ሁለቱ ቡድኖች ሁለት ጊዜ ተገናኝተው ባህርዳር በሜዳው 2-0፤ ሽረ በሜዳው 1-0 አሸንፈዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህርዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪስተን ሄሱ

ሳላአምላክ ተገኘ – አዳማ ሲሴኮ – አቤል ውዱ – ሚክያስ ግርማ

ዳንኤል ኃይሉ – ሳምሶን ጥላሁን – ፍፁም ዓለሙ

ፍቃዱ ወርቁ – ስንታየሁ መንግሥቱ – ግርማ ዲሳሳ

ስሑል ሽረ (4-2-3-1)

ምንተስኖትአሎ

ዐወት ገብረሚካኤል – በረከት ተሰማ – አዳም ማሳላቺ – ረመዳን የሱፍ

ነፃነት ገብረመድኅን – ሀብታሙ ሽዋለም

መድሀኔ ብርሀኔ – ያሳር ሙገርዋ – ዓብዱለጢፍ መሐመድ

ሳሊፍ ፎፋና

© ሶከር ኢትዮጵያ