ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

በ3ኛ ቀን የ15ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር የሚገናኙት ሀዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ መቐለ አምርተው 5-1 የተሸነፉት ሀዋሳ ከተማዎች ደግም ወደ አሸናፊነት በመመለስ የሊጉን አጋማሽ ለማገባደድ እና በተከታታይ የሜዳቸው ላይ ጨዋታዎች ያገኙትን ጥንካሬ ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።

የሀዋሳ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ አሸነፈ ተሸነፈ

ወጣ ገባ አቋም ከሚያሳዩ የሊጉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆኑት ሀዋሳ ከተማዎች በየጨዋታዎቹ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ እና የሚያስመዘግቡት ውጤት እጅግ የማይገመት ሆኗል። በተለይ ክለቡ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ሲጫወት የሚከተለው የጨዋታ መንገድ መለያየቱ ቋሚ የጨዋታ አቀራረቡን እንዳይገመት አድርጎታል።

ባለፉት ጨዋታዎች ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው በጉዳት አጥተው የነበረው ሀይቆቹ በነገው ጨዋታ የመስፍን ታፈሰን ግልጋሎት ማግኘታቸው ጥሩ ነው። ይህ ተጨዋች ፍጥነቱን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አደገኞች ስለሆነ ነገ ፋሲሎች ሊቸገሩ ይችላሉ። ስለሆነም ይህ ተጨዋች ከወጣቱ አጥቂ ብሩክ በየነ ጋር የቡድኑን የፊት መስመር በመምራት ግቦችን ለማስቆጠር እንደሚጥር ይገመታል። በተለይ ተጨዋቾቹ ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ ግቦችን ለማስቆጠር ስለሚጥሩ ፋሲሎች ሊፈተኑ ይችላሉ። 

ይህ እንዳለ ሆኖ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አለልኝ አዘነ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አለመኖሩ ቡድኑን በመጠኑ ሊጎዳ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ብዙ ጥገናዎች እንደሚያስፈልጉት በመቐለው ጨዋታ ታይቷል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ለአስፈሪው የፋሲል የፊት መስመር ቡድኑ በጎ ነገሮችን ሊቸር ይችላል።

እስራኤል እሸቱ አሁንም ጉዳት ላይ ሲገኝ አለልኝ አዘነ በመቐለው ጨዋታ በተመለከው ቀይ ካርድ ምክንያት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል። ነገር ግን ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ርቆ የነበረው መስፍን ታፈሰ በሙሉ ጤነኝነቱ ላይ በመገኘቱ ለጨዋታው ዝግጁ ነው ተብሏል።

የፋሲል ከነማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ)
አቻ አሸነፈ አሸነፈ አቻ አሸነፈ

ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ፋሲል ከነማዎች ጥር 30 ወደ መቐለ አምርተው ያገኙትን የዓመቱን ብቸኛ የሜዳው ውጪ ድል ለመድገም እና የሊጉ አናትን ለመቆናጠጥ 9 ሰዓትን ይጠብቃሉ።

የሊጉ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑት ፋሲል ከነማዎች በነገው ጨዋታ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይ የሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ምቹነት ቡድኑን እንደልቡ ኳስ እንዲያንሸራሽር እንደሚያደርገው ይታሰባል። ከምንም በላይ ግን የአማካይ መስመር ተጨዋቾቹ ብቃት ቡድኑን ነገ ተጠቃሚ ሊያደርግ ይችላል። በዚህም ሱራፌልን ጨምሮ ቡድኑ ውስጥ ያሉት የአማካይ እና የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ለሊሉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሙጂብ ጥሩ እድሎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመላክ ግብ ለማስቆጠር እንደሚታትሩ ይታሰባል።

ከኳስ ቁጥጥር ውጪ የቆሙ ኳሶችን፣ ፈጣን ሽግግሮችን እና ረጃጅም ኳሶችን በማዳቀል ለጨዋታ የሚቀርቡት ዐፄዎቹ በነገውም ጨዋታ እንደ ሃዋሳ አቀራረብ ስላታቸውን ሊለዋውጡ ይችላሉ። በተለይ ግን የቡድኑ አስፈሪ አጥቂን (ሙጂብ) ያነጣጠሩ ኳሶች ከመስመር በመላክ የሀዋሳዎችን ጊዜ ከባድ ለማድረግ ይጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሊጉ ሁለተኛው ብዙ ጎል ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠረ ክለብ የሆነው ፋሲል (23) የኋላ መስመሩም እንደ ፊት መስመሩ ጠንካራ ነው። በተለይ የቡድኑ አምበል ያሬድ ወደ ጨዋታዎች መመለሱ ቡድኑን ከፍተኛ የራስ መተማመን አላብሶታል። ነገር ግን ቡድኑ በተከላካይ እና በአማካይ መስመር መካከል ኪሶችን ለተጋጣሚ ሲሰጥ ይስተዋላል። ምናልባትም ይህንን ችግር ቡድኑ በነገው ጨዋታ የማያስተካክል ከሆነ ሃዋሳዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ።

በቅጣት ሽመክት ጉግሳን የማያሰልፈው ቡድኑ ኦሴ ማውሊንም አያሰልፍም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ፋሲል ከነማ ወደ ሊጉ በ2009 ከተመለሰ በኋላ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ሀዋሳ 2 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ፋሲል 1 አሸንፏል። በሦስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ሀዋሳ 10፣ ፋሲል 8 አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሃዋሳ ከተማ (4-2-3-1)

ቢሊንጋ ኢኖህ

ዳንኤል ደርቤ – መሳይ ጳውሎስ – ላውረንስ ላርቴ – ያኦ ኦሊቨር

ተስፋዬ መላኩ – ሄኖክ ድልቢ

አክሊሉ ተፈራ – ዘላለም ኢሳይያስ – መስፍን ታፈሰ

ብሩክ በየነ

ፋሲል ከነማ (4-3-3)

ሚካኤል ሳማኬ

እንየው ካሳሁን – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየ – አምሳሉ ጥላሁን

በዛብህ መለዮ – ጋብሬል አሕመድ – ሱራፌል ዳኛቸው

ዓለምብርሀን ይግዛው – ሙጂብ ቃሲም – አዙካ ኢዙ

*በኤዲት የተስተካከለ

© ሶከር ኢትዮጵያ