ወልዋሎዎች ከአስራ ዘጠኝ ወራት በኋላ ወደ ሜዳቸው ተመልሰው የሚያደርጉት ጨዋታን እንደሚከተለው ዳሰነዋል።
ባለፉት ሳምንታት በተከታታይ ነጥብ ጥለው ከደረጃቸው የተንሸራተቱት ወልዋሎዎች ከ19 ወራት የመቐለ ቆይታቸው በኃላ በሜዳቸው በሚያደርጉት ጨዋታ አሸንፈው ደረጃቸው ለማሻሻል አስበው ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የወልዋሎ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | ተሸነፈ | አቻ |
ብልጫ ወስደው የተጫወቱባቸው ጨዋታዎች ጭምር ማሸነፍ አቅቷቸው የቆዩት ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ ሦስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ከጉዳት መልስ ማግኘታቸው ለቡድኑ ጥሩ ዜና ነው። በተለይም የዓይናለም ኃይለ እና ፍቃዱ ደነቀ መመለስ ያለወትሮው ተዳክሞ በርካታ ግቦች ላስተናገደው የቡድኑ ተከላካይ መስመር ጥንካሬ ያላብሳሉ ተብሎ ሲጠቅበ በአስገዳጅ ሁኔታ ካለቦታቸው የተሰለፉት ተጫዋቾችም ወደ ተፈጥሯዊ ቦታቸው ይመለሳሉ ተብሎ ይገመታል።
ከባለፉት ጨዋታዎች በተሻለ በርካታ የተጫዋቾች ምርጫ ያላቸው የቡድኑ ግዜያዊ አሰልጣኞች አብርሀ ተዓረ እና ኮማንደር ኪዳነ ሀፍተ ከቀጥተኛው አጨዋወት ወጣ ያለ አቀራረብ ሊኖራቸው እንደሚችል ይታሰባል። ከዚ በተጨማሪ ባለፉት ጨዋታዎች የሚፈጠሩትን ንፁህ የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ትልቅ ክፍተት የነበረበት የጁንያስ ናንጂቡ እና ኢታሙና ኬይሙኔ ጥምረት አጋጣሚዎችን የመጠቀም አቅማቸው ማሻሻል በጨዋታው ላይ ውጤት የመቀየር አቅሙ ትልቅ ነው። በተለይም ጁንያስ ናንጂቡ የአጨራረስ አቅሙ ካሻሻለ ለቡድኑ ነገሮችን ቀላል ያደርግለታል።
ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በላይ በነገው ጨዋታ ወደ ድል ለመመለስ የደጋፊው ኃይል ትልቅ ቦታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል። ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ሜዳቸው እንደመመለሳቸው በደመቀ ድጋፍ እና በከፍተኛ ተነሳሽነት ታግዘው ጨዋታውን ማድረጋቸው አይቀሬ ነው።
ወልዋሎዎች በነገው ጨዋታ ሰመረ ሀፍታይን በጉዳት ስያጡ አቼምፖንግ አሞስ ፣ ፍቃዱ ደነቀ እና አይናለም ኃይለ ከጉዳት ተመልሰውላቸዋል። ቀላል ልምምድ የጀመረው ካርሎስ ዳምጠውም ለጨዋታው ብቁ ከሆነ በስብስቡ ይካተታል ተብሎ ይጠበቃል።
የወልቂጤ ከተማ ያለፉት 5 ጨዋታዎች አቋም (ከቅርብ ወደ ሩቅ) | ||||
ተሸነፈ | አቻ | አሸነፈ | አሸነፈ | አሸነፈ |
በውጤት አልባው አጀማመር በኃላ ወደ ጥሩ ብቃት መጥተው በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ አግኝተው ደረጃቸውን አሻሽለው የነበሩት ወልቂጤዎች ተከታታይ ሽንፈት ይዞባቸው ከሚመጣው የወራጅ ቀጠና ስጋት ለመላቀቅ ነጥብ ማግኘትን አልመው ወደ ጨዋታው ይገባሉ።
ተለዋዋጭ አቀራረብ ያላቸው ሰራተኞቹ ከሜዳቸው ውጭ እንደሚከተሉት አጨዋወት በዚህ ጨዋታም ቀጥተኛ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ሲጠበቅ እንደ ተጋጣሚው አቀራረብ ሁኔታም በጨዋታው መሀል አጨዋወታቸው ላይ ለውጥ የሚያደርጉበት ዕድል የሰፋ ነው። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቀስ ደግሞ ቡድኑ ኳስ ተቆጣጥሮ በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ እና ተጋጣሚው ወልዋሎ ለኳስ ቁጥጥር ቅድምያ ሰጥቶ ይጫወታል ተብሎ ስለማይገመት ነው።
ሰራተኞቹ ፍፁም ተፈሪን በጉዳት ሲያጡ ይበልጣል ሽባባው ከጉዳት ተመልሶላቸዋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወልዋሎ (4-2-3-1)
ዓብዱልዓዚዝ ኬታ
ምስጋናው ወ/ዮሐንስ – አቼምፖንግ አሞስ – ዓይናለም ኃይለ – ሳሙኤል ዮሐንስ
ገናናው ረጋሳ – ፍቃዱ ደነቀ
ብሩክ ሰሙ – ራምኬል ሎክ – ኢታሙና ኬይሙኔ
ጁንያስ ናንጂቡ
ወልቂጤ (4-3-3)
ይድነቃቸው ኪዳኔ
ዳግም ንጉሴ – ቶማስ ስምረቱ – ዐወል መሐመድ – አዳነ በላይነህ
አሳሪ አልማህዲ – በረከት ጥጋቡ – ኤፍሬም ዘካርያስ
ጫላ ተሺታ – አሕመድ ሁሴን – ሳዲቅ ሴቾ
© ሶከር ኢትዮጵያ