የአሰልጣኞች አስተያየት| ሲዳማ ቡና 1-0 ሰበታ ከተማ

በአስራ አምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲዳማ ቡና በሜዳው ሰበታ ከተማን አሰሠተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ተሰጥተዋል።

”ብዙ አጋጣሚውን አግኝተን ነበር፤ አለመጠቀማችን ጨዋታውን ትንሽ አክብብዶናል” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ኳስን መሰረት ያደረገ እጅግ በጣም ጥሩ ጨዋታ ነው። ደጋፊዎች ተደስተው እንደሄዱ አምናለሁ። ወደፊት በመሄድ የተሻልን ነበርን፤ ብዙ አጋጣሚውን አግኝተን ነበር፤ አለመጠቀማችን ትንሽ ከብዶናል። ያም ሆኖ ግን ከእረፍት በኋላ ባስቆጠርነው ግብ ሦስት ነጥብ መውሰድ ችለናል። በጣም አሪፍ እና ጠንካራ ጨዋታ ነበር።

ስለመጀመሪያው ዙር እና ቀጣይ ዙር

አንደኛው ዙር ላይ በተለይ ሁለቱ የመጨረሻ ጨዋታዎች ላይ ወደ መከላከሉ ያመጣናቸው የአጨዋወት ስትራቴጂ ከዘህ በፊት ተግብረናቸው ቢሆን የተሻለ ነጥብ እናመጣ ነበር። በሁለተኛው ዙር ላይ የተሻላ ተጠናክረን ጥሩ ቡድን ይዘን እንቀርባለን ብየ አስባለሁ። መጀመሪያ ላይ የነበረን ክፍተት ወደ መከላከሉ ነበር። በሁለቱ ጨዋታዎች ላይ አስተካክለናል። ያንን ደግሞ ለማስቀጠል ጥረት እናደርጋለን።

ተጫዋቾችን እያፈራረቁ ስመጠቀም

እስካሁን ከነበረው ጥሩ ነው። ግን ያም ሆነ ይህ ቡድናችንን ማጠናከር አለብን። ተጨማሪ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናችን በመቀላቀል የተሻለ እናጠናክራለን ።

”በከባድ ፀሐይ ጎማ ላይ መጫወት በጣም ከባድ ነው፤ በተለይ ለኛ ሜዳውን ለማናውቀው ” ውበቱ አባተ (ሰበታ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

ከባድ ጨዋታ ነው። ከሜዳው አንፃር በብዙ ነገሮች ጠንካራ ጨዋታ ነው። አሪቲፊሻል ሜዳ ላይ ነበር፤ በተለይ ከእረፍት በፊት ከባድ ፀሃይ ነበር። ጎማ ላይ መጫወት በጣም ከባድ ነው፤ በተለይ ለኛ ሜዳውን ለማናውቀው። በዛ ላይ ሲዳማን ነው የገጠምነው። ያም ሆኖ ግን ጥሩ ነበርን። ግን 1-0 ተሸንፈናል የምንችለውን ለማድረግ እስከ መጨረሻው ተፎካክረናል። ያው ወጤቱን መቀበል ነው ።

ስለ ዳኝነቱ እና ስለ ቀይ ካርዱ

ቀዩ ካርድ ለምን እንዳሳየው አለውቅም። በሁለተኛ ቢጫ ይሁን ቀጥታ ይሁን አላውቅም። መጀመሪያ ቢጫ ያየበት ሁኔታ ግን በፍፁም ቢጫ የሚያሳይ ሁኔታ አይደለም። ኳስ ወደ ውጭ ሲወጣ የሚያመላልሱ ታዳጊዎች የሉም። ኳስ አመላላሾቹ በየሜዳው ፍትሃዊ አይደሉም፤ ህፃናቶች ናቸው ግን ምን እንደሚያስቡ አላውቅም። ክለባቸው መምራቱን ተከትሎ ኳስ ያዘገዩ ነበር። ያንን ኳስ ከውጭ አምጥቶ እንዲጀመር ነው ያስቀመጠው ሌላ ያደረገው ነገር የለም። የመጀመሪያው ቢጫ አግባብ ነው ብዬ አላስብም። ከዛ ውጭ ያለው ነገር ግን የዳኛው ውሳኔ ነው፤ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም።

የ15 ሳምንታት ጉዞ

ያው ከታች እንደመጣ ቡድን አብዛኛው ጨዋታ በሜዳችን ያለውንም ከሜዳ ውጭ ነው። ከዛ አንፃር የተሻለ ነጥብ ብንሰበስብ ጥሩ ነበር። በነጥብ ደረጃ ግን የያዝነው ነጥብ በቂ አይደለም። ከዚህ በላይ ይዘን ማጠናቀቅ ነበረብን። ሁለተኛው ዙር ላይ ያሉብነን ክፍተቶች አስተካክለን የተሻለ ነገር ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ