U-20 ምድብ ሀ | ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ሲንበሸበሹ ሲዳማ እና ጥሩነሽም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ሁሉም ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ በምድብ ሀ ሀዋሳ በሜዳው ወላይታ ድቻ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎሎች አዝንቧል። ቅዱስ ጊዮርጊስም በግብ ሲንበሸበሽ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሲዳማ ቡና ድል አስመዝግበዋል።

4:00 ሲል ጠንከር ባለ ፀሀይ የጀመረው የሀዋሳ እና ድቻ ጨዋታ በባለሜዳው 6-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሙሉ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ ለተመልካቹ ማራኪ የሆነ እንቅስቃሴ በግብ ታጅቦ ያየንበት ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች ኳስን ከመረብ ጋር በማዋሀዱ ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ። ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው በእንቅስቃሴ እና በቅብብሎች ተሽለው ቢታዩም የሀዋሳ የግብ ክልል ሲጠጉ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል አልፎ ለመግባት ግን ሲሳናቸው አስተውለናል፡፡ 

ገና 4ኛው ደቂቃ ላይ ምስክር መለሰ ባስቆጠራት ግብ ድቻዎች መሪ ቢሆኑም የተከላካይ መስመራቸው በትክክል መጠበቅ ባለመቻላቸው ግብ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ ዳግም ፀጋዘአብ እና አስመላሽ ዓለማየሁ አከታትለው ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ወደ መሪነት የተሸጋገሩት ሀዋሳዎች የድቻን ክፍተት አሁንም በሚገባ መጠቀማቸውን ቀጥለው በፍፁም ቅጣት ምት በሮቤል ግርማ ተጨማሪ ግብ አክለው 3ለ1 ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ድቻዎች የእንቅስቃሴ ወጥነት ቢኖራቸውም ለመከላከል ያላቸው ደካማነትን ሊቀርፉ አሁንም አልቻሉም 56ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን በቀለ ብልጠቱን ተጠቅሞ የሰጠውን ኳስ ዳግም ፀጋዘአብ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ከመልሶ ማጥቃት ውጪ በድቻ የተበለጡት ሀዋሳዎች አጨራረስ ላይ የነበራቸው ውሳኔ ግን አስገራሚ ነበረ፡፡ 76ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀኝ በኩል ያሻገረለትን ብሩክ አለማየሁ ወደ ግብነት ለውጦ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ አምስት ከፍ አድርጓል፡፡

በታምራት ስላስ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ወደ ጨዋታ የተመለሱ የመሰሉት ድቻዎች ተጨማሪ ግብ ተቆጥሮባቸዋል፡፡ ጨዋታ ተጠናቆ ሽርፍራፊ ሰከንድ ላይ እጅግ ማራኪ የቅጣት ምት ጎል ሙሉቀን ታደሰ ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው በሀዋሳ 6ለ2 ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የእለቱ ዳኛ የድቻው አማካይ መሳይ ኒኮል ከላይ ያደረገው መለያ ተቀዶ ለረጀም ሰአት ሲቆይ በዝምታ ማለፋቸው አስገራሚ ነበር፡፡

በሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና መከላከያን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል። ዳመነ ደምሴ እና በፍቅር ጌታቸው የጎሎቹ ባለቤት ናቸው።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 4-1 መርታት ችሏል። ፀጋዬ አበራ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ዳግማዊ አርዓያ እና በረከት ማሕተቤ ቀሪዎቹን አስቆጥረዋል። ሚካኤል ሰሎሞን የድሬ ብቸኛ ጎል አስቆጣሪ ነው።

ኢ/ወ/ስ/አካዳሚ በሜዳው በጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 1-0 ተሸንፏል። አማኑኤል አድማሱ ብቸኛ ጎል አስቆጣሪ ነው። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ በዚህ ሳምንት አራፊ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ