U-20 ምድብ ለ | ፋሲል እና አዳማ ከሜዳቸው ውጪ፤ አሰላ ኅብረት በሜዳው አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ፋሲል፣ አዳማ እና አሰላ ኅብረት አሸንፈዋል።

ጎፋ በሚገኘው የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሜዳ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማ ተገናኝተው እንግዶቹ 2-0 አሸንፈዋል። ጥሩ ፍሰት ያለው እግርኳስ በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉ ነበሩ። በተለይ ዓምና ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፈው አጥቂው በረከት ብርሀኑ በጥሩ መንገድ የተቀበለውን ኳስ ወደ ጎል መቶት የዐፄዎቹ ግብጠባቂ መንገሻ አየሩ ያዳነበት የመጀመርያው ሙከራቸው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ራሱ በረከት ብርሃኑ ከመሐል ሜዳ የተጣለለትን ኳሱ አየር ላይ እያለ የግብጠባቂውን አቋቋም አይቶ ወደ ጎል ቺብ አድርጎ ቢነታውም ለጥቂት ወጥቶበታል። ጥሩ እግርኳስ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የተሰባሰቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በመጀመርያዎቹ የጨዋታ ጅማሬ ያገኙትን ግልፅ የጎል አጋጣሚዎች አለመጠቀማቸው ጨዋታውን በቀሪዎቹ ደቂቃዎች እንዳይቆጣጠሩ አድርጓቸዋል። ወደ ጨዋታውን አንቅስቃሴ ለመግባት ለጊዜው ቢቸገሩም ኃላ ላይ እየተነቃቁ የመጡት ዐፄዎቹ ብልጫ ወስደው መጫወት ብቻ አይደለም አስደናቂ ጎል ማስቆጠር ችለዋል።

ጎሉ የተቆጠረበት የኳስ ንክኪ ከእነርሱ ሜዳ ጀምሮ አንድም ሳይቋረጥ ከመስመር ወደ መሐል ሰብረው በመግባት የወደፊት የፋሲል ከነማ ተስፈኛ ተጫዋች መሆን እንደሚችል የተመለከትነው ፋሲል ማረው ተከላካዮችን ግብጠባቂውን በድጋሚ ተከላካይ በማለፍ አስደናቂ ጎል በ25ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

የነበራቸው ፍጥነት ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኃላ ቀዝቀዝ ያሉት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ኳሱ እየተበላሸ በቀላሉ በፋሲል ከነማ ተከላካዮች እየተነጠቁ ኳሶቻቸው ይቋረጡ ነበር።

እግራቸው ውስጥ ኳሶቹ ሲገቡ ወደ ማጥቃት ሽግግር የሚገቡበት መንገድ አስገራሚ የነበረው የፋሲሎች ከእረፍት መልስ ወድያውኑ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ከመስመር ሲያሻግሩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ተቀይሮ የገባው ሙከሪም ረሺዲ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል የፋሲልን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

በቀሪው ደቂቃዎች ፋሲሎች ከሁለት ጎል በላይ ጎሎች ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድሎች በመልሶ ማጥቃት በሚፈጥሩት ሳይጠቀሙ ቀርተው በኢትዮ ኤሌክትሪኮች በኩል በተለይ አንበሉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሄኖክ ማኀቶት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ለወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች እንደሆነ ከመመልከት ውጭ የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን ጨዋታው በአንግዶቹ ፋሲሎች 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ወደ ሱሉልታ የተጓዘው አዳማ ከተማ በምዑዝ ሙኅዲን ብቸኛ ጎል ሱሉልታ ከተማን 1-0 አሸንፎ ሲመለስ አሰላ ኅብረት በሜዳው ወልቂጤ ከተማን በበድሩ ከማል ጎል 1-0 አሸንፏል። አዲስ አበባ ከተማ 1-1 ኢትዮጵያ መድን ኢብራሒም ሰንበቶ ለአአ፤ ጌታሁን ካሕሳይ ለመድን ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ሀላባ ከተማ የዚህ ሳምንት አራፊ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ