ቅዳሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በተደረገው ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ አካላት ክለቡን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።
ቴሌቶኑ ክለቡ ካጋጠመው የገንዘብ ችግር ለማገገም እንዲረዳው እና ለተጨዋቾች ደሞዝ፣ ለካምፕ ማደሻ እንዲሁም ለተለያዩ ወጪዎች እንዲሆን ዘንድ ታቅዶ መዘጋጀቱ ተነግሯል። በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ በተደረገው በዚህ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ የመንግስት አመራሮች እና የግል ባለሃብቶች ተገኝተዋል።
በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይም የተለያዩ የመንግስት አካላት፣ የግል ሆቴሎች፣ የውሃ መጠጥ ፋብሪካዎች፣ የህዝብ ማመላለሻ ባስ አክሲዮን ማህበሮች፣ የሪል እስቴት ድርጅቶች፣ የቀለም ፋብሪካዎች፣ የኮንስትራክሽን ተቋማት እና ሌሎች የክለቡ ደጋፊዎች በቦታው በአካል በመገኘት እና በስልክ በመደወል ገንዘብ እንደሚለግሱ ቃል ገብተዋል። የእነዚህን እና የተለያዩ ግለሰቦችን እንሰጣለን ያሉትን ቃል በመደመርም ክለቡ ከትናንትናው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ቃል እንደተገባለት ለማወቅ ተችሏል። ከዚህ ውጪ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለክለቡ የመጓጓዧ ባስ በቅርቡ እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።
በዚህ ቴሌቶን ብቻ የማያበቃው የክለቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በቀጣይ የጎዳና ሩጫዎች እና የሙዚቃ ኮንሰርቶች በባህር ዳር በማከናወን ክለቡን በፋይናንስ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተነግሯል።
© ሶከር ኢትዮጵያ