በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 15ኛ ሳምንት ሦስተኛ የጨዋታ ቀን ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ምዓም አናብስትን አስተናግዶ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
ድሬዳዋ ባለፈው ሳምንት በጅማ ከተሸነፈው ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በበረከት ሳሙኤል ምትክ ያሬድ ዘውድነህን፤ በዋለልኝ ገብሬ ምትክ ደግሞ ፈርሀን ሰዒድን በማሰለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። መቐለዎች በአንፃሩ ባለፈው ሳምንት ሀዋሳን ከረመረሙበት አሰላለፍ በያሬድ ከበደ ምትክ ከቅጣት የተመለሰው ዳንኤል ደምሴን ብቻ ወደ ሜዳ ቀይረው በማስገባት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።
በመጀመርያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች በተጋጣሚያቸው የሜዳ አጋማሽ አመዝነው ኳሶችን ሲያንሸራሽሩ እንግዶቹ በአንፃሩ በረጅም ኳሶች የጎል እድል ለመፍጠር ጥረዋል። ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ድሬዎች በ4ኛው ደቂቃ ፈርሀን ሠዒድ አስራ ስድስት ከሀምሳ ውስጥ የመቐለ ተከላካዮች አልፎ አደጋ ሳይፈጥር በመቐለ ተከላካዮች ርብርብ በተቋረጠው ኳስ ጥቃት ሲሰነዝሩ በ19ኛው ደቂቃ ሪቻሞንድ ኦዶንጎ በግምት 20 ሜትር ላይ ሆኖ የመታት የግቡን የላይኛ አግዳሚ ታካ ወጣች እንጂ መሪ መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ነበረች።
በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት ተቸግረው የታዩት መቐለዎች ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ እንቅስቃሴ ቢመለሱም በርከት ያለ የጠራ የግብ እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። ጨዋታው ብዙ ሳይጓዝም ጉዳት የገጠመው አሌክስ ተሰማን በማውጣት ላውረንስን ወደ ሜዳ በማስገባት ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። ቡድኑ በመጀመርያው አጋማሽ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በ23ኛው ደቂቃ ነበር፤ ኦኪኪ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው አድኖበታል።
ጨዋታው ቀጥሎ ብሩቱካናማዎቹ መሪ ሊሆኑ የሚችልበትን ዕድል በ33ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። ፈርሀን ያቀበለውን ኳስ ኤልያስ ማሞ ከሩቅ መትቶ አግዳሚውን ጨርፋ የወጣችበት፤ በተጨማሪም በ40ኛው ደቂቃ ያሲን ጀማል ከርቀት የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ የወጣበት አጋጣሚ የምትጠቀስ አስቆጪ እድል ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተስዋለበት ነበር። በ47ኛው ደቂቃ የምዓም አናብስቱ ቡድን ወሳኝ ተጫዋች አማኑኤል ገብረሚካኤል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከርቀት በግራ እግሩ የመታው ኳስ በአግዳሚው ለጥቂት ከፍ ብሎ ወጥቶበታል። በድጋሚ በ67ኛው ደቂቃ አማኑኤል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
በዛሬው ጨዋታ በሁለቱም ተጋጣሚዎች የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ሳጥን ውስጥ ከሚሞከሩት ይልቅ ከርቀት የሚሞከሩት ሚዛን ደፍተው የታዩበት ነበር። በዚህም ድሬዎች ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ግብ ፍለጋቸውን ቀጥለው በ51ኛው ደቂቃ ሙህዲን አንድ ተከላካይን ቀንሶ የመታው ብረቱን ታኮ ሲወጣበት 70ኛው ደቂቃ ላይ አማረ በቀለ በቀጥታ የመታት ኳስ ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣበት እንዲሁም በ84ኛው ደቂቃ ላይ ፈርሀን ከአማረ በቀለ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ለወጠው ተብሎ ሲጠበቅ በቀላሉ ያባከነው የሚጠቀሱ ነበሩ።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በሄደ ቁጥር እጅግ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ጨዋታው በዚሁ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት ድሬዎች ውድ ሦስት ነጥቦች ያገኙበትን ጎል አግኝተዋል። ከማዕዘን መነሻ አድርጎ የተሻማውን ኳስ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው ዳኛቸው በቀለ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታውም በድሬዳዋ ከተማ 1-0 በሆነ አሸናፊነት ውጤት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ መቐለ በጊዜያዊነት ሊጉን የሚመራበትን እድል ሲያባክን ድሬዳዋ ከወራጅ ቀጠናው ባይወጣም አንድ ደረጃ አሻሽሎ ከበላዩ ካሉት ቡድኖች ያለውን ልዩነት ማጥበብ ችሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ