የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-0 ስሑል ሽረ

በባለሜዳዎቹ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የባህር ዳር ከተማ እና የስሑል ሽረ ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።


“የሜዳ ላይ ሪከርዳችንን በማስጠበቃችን ደስተኛ ነኝ” ፋሲል ተካልኝ (ባህር ዳር ከተማ)

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ጥሩ ጨዋታ ነበር። በቅድሚያ የሜዳ ላይ ሪከርዳችንን ማስጠበቅ እንፈልግ ነበር። ይህም ተሳክቶልናል። ተጋጣሚያችን ጠንካራ የመከላከል ስልት ነበር ሲከተል የነበረው። ከዚህ በተጨማሪም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችንም ሲተገብር ነበር። እኛም ይህንን ታሳቢ አድርገን ነበር ስንጫወት የነበረው። በአጠቃላይ በምንፈልገው መንገድ ለማጥቃት ሞክረናል። ነገር ግን የመጨረሻው የማጥቃት ወረዳ ላይ ስንደርስ የነበረን ውጤታማነት ጥሩ አልነበረም። የሆነው ሆኖ ግን ጨዋታውን በማሸነፋችን ደስ ብሎኛል።

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተከተሉት ጥንቃቄ አዘል እንቅስቃሴ?

አንዳንድ ጊዜ ጨዋታዎች በሁለተኛው አጋማሽ ለውጦችን እንድታደርግ ያስገድዱሃል። በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን ረጃጅም ኳሶችን ከመሃል እና ከመስመር እየላከ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። በዚህ ውስጥም ሆነን ግን ለማጥቃት ፍላጎቶች ሲናሳይ ነበር። ከምንም በላይ ግን አንድ ጎል አስተማማኝ ስላልሆነ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጨዋታዎች ጎላችንን ከፍተን መጫወት አልፈለግንም።

ቡድኑ ከረጅም ጊዜ በኋላ ግብ ሳያስተናግድ ስለመውጣቱ እና እንደተለመደው ቡድኑ ብዙ ጎሎችን በሜዳው ስላላስቆጠረበት ምክንያት?

ግብ ሳይገባብን ጨዋታውን መጨረሳችን ለተከላካዮቼ የስነልቦና እገዛ ያደርጋል። እኔ ግን በተፈጥሮዬ አንድ ለዜሮ ከሚያሸንፍ ቡድን ሶስት ለሁለት የሚያሸንፍ ቡድን ቢኖረኝ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም ተመልካች ወደ ስታዲየም የሚመጣው ሊደሰት ነው እና ግቦች መግባት አለባቸው። ይህንን ስል ግን የመከላከሉ ላይ ያለንን ክፍተት ለመሸፈን እየሞከርኩ አይደለም።

በመጀመሪያው ዙር ቡድኑ ስላደረገው እንቅስቃሴ?

ቡድናችን ላይ ያሉትን ነገሮች ከተጨዋቾቼ ጋር ቁጭ ብለን የምንነጋገርበት ይሆናል። ግን በጠቅላላው ጥሩ የሚያጠቃ እና ጎል የሚያስቆጥር ቡድን አለን። በተቃናኒው ደግሞ የመከላከል ስህተቶች እና በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ራሳችን የግብ ክልል የማፈግፈግ ችግር ይታይብናል። ከዚህ ውጪ ከሜዳችን ውጪ የምናደርጋቸውን ጨዋታዎች ማሸነፍ መጀመር አለብን። በቀጣይ እነዚህን ነገሮች አስተካክለን በሁለተኛ ዙር ለመቅረብ እንሞክራለን።

“በሁለተኛው አጋማሽ ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ መቀየር ባለመቻላችን ተሸንፈናል” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው?

ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ ነጥብ ላይ መገኘታቸውን ተከትሎ ጨዋታው ውጥረት የበዛበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ባህር ዳሮች ተጭነውን ለመጫወት ሞክረዋል። በተቃራኒው ደግሞ እኛ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነን ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ነገር ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ መቀየር አልቻልንም። እንደ አጠቃላይ ግን የነበረው ጨዋታ ጥሩ ነበር።

ቡድኑ ስለነበረው እቅድ?

በመጀመሪያው አጋማሽ በነበሩት 20 እና 30 ደቂቃዎች ባህር ዳር ግብ እንዳያስቆጥርብን ነበር የጣርነው። ከዛም በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ በማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር ነበር አስበን የገባነው። ይህንንም የመረጥነው ስለ ባህር ዳር ከሰማነው መረጃ አንፃር ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ስጋት የነበረብን የቆሙ ኳሶችን እንዳይጠቀሙብን ነበር። ነገር ግን እነሱ በቆመ ኳስ ግብ አስቆጥረውብን ተሸንፈናል።

ስለ ቡድኑ የዓመቱ አጋማሽ እንቅስቃሴ?

ጥሩ ነበር። ዓምና ከነበሩብን ክፍተቶች መነሻነት ስራዎችን ቀድመን ስንሰራ ነበር። በሁለተኛ እና ሶስተኛ ሳምንት ያስመዘገብነው ውጤት ጥሩ አልነበረም። ከዛ ተነስተን ግን በሜዳችንም ሆነ ከሜዳችን ውጪ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ጥረናል። አልፎ አልፎ የአጨራረስ ችግር ይታይብናል። በአጠቃላይ ግን ጥሩ አመጣጥ ነው የመጣነው። በቀጣይ ክፍተቶቻችንን አሻሽለን ለሁለተኛ ዙር እንቀርባለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ