በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስራ አምስተኛው ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ፋሲል ከነማን አስናግዶ ሁለት ለዜሮ ከመመራት ተነስቶ 3ለ2 በመርታት ወሳኝ ሙሉ ነጥብ አግኝቶ ዙሩን ፈፅሟል፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የመገናኛ ብዙሀን በተለይ ካሜራ የያዙ ወደ ቅጥር ግቢው አትገቡም በሚል የእለቱ አራተኛ ዳኛ አዳነ ወርቁ ከጋዜጠኞች ጋር የፈጠሩት አሰጣ ገባ ያልተለመደ አይነት የነበረ ሲሆን ጋዜጠኞችን በተመልካቹ ፊት ያዋከቡበት ድርጊት ያልተገባ ነበር። በስተመጨረሻ ግን የኢትዮጵያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር ተወካይ ሚካኤል አርዓያ እና ሌሎች ግለሰቦች ለጋዜጠኞች ቦታ በማመቻቸት ባደረጉት መልካም ተግባር የተመረጡ ጋዜጠኞች ገብተው መከታተል ችለዋል፡፡
ሀዋሳዎች ባለፈው ሳምንት በመቐለ በሰፊ ጎል ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ውስጥ ከግማሽ በላዩ ላይ ቅያሪን አድርገዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቢሊንጌ ኢኖህን በሀብቴ ከድር፣ ወንድማገኝ ማዕረግን በዳንኤል ደርቤ፣ አለልኝ አዘነን በአስጨናቂ ሉቃስ፣ ፀጋአብ ዮሀንስን፣ በዘላለም ኢሳያስ፣ ብርሀኑ በቀለን በመስፍን ታፈሰ እንዲሁም የተሻ ግዛውን በሄኖክ ድልቢ ለውጠው ጀምረዋል፡፡ በዐፄ ፋሲለደስ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግደው ነጥብ ተጋርተው የመጡት ዐፄዎቹ በቅጣት የሌለው ሽመክት ጉግሳን በሀብታሙ ተከስተ፣ እንየው ካሳሁንን በሰዒድ ሀሰን ተክተዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በመሩት በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ፋሲሎች በሜዳቸው የሚጫወቱ ይመስሉ ነበር። ሀዋሳዎች በቅብብል በፍጥነት ወደ ፋሲል ግብ ክልል ሲደርሱ መሀል ላይ የተቋረጠችው ኳስ ከመረብ ገና በጊዜ መዋሀዷም አጀማመራቸውን እንዲያሳምሩ ረድታቸው ነበር፡፡ 4ኛው ደቂቃ ላይ ከአንድ ሁለት የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ወደ ሀዋሳ ግብ ክልል የደረሱት ዐፄዎቹ በዛብህ መለዮ ሰቶት ኢዙ አዙካ በቀጥታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ በማራኪ ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ግብ ለማስናገድ የተገደዱት ባለሜዳዎቹ በተለይ ዳንኤል ደርቤ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ለመጠቀም ከተሻጋሪ አልያም በአንድ ሁለት የጨዋታ መንገድ ተከትለው በሁለቱ ወጣት አጥቂዎች መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ ድንቅ ጥምረት ምላሽ ለመስጠት ጥረት አድርገዋል፡፡ 6ኛው ደቂቃም መስፍን ታፈሰ በግራ በኩል የሰጠውን ኳስ ብሩክ በየነ መረጋጋት ተስኖት ሳይጠቀምበት የቀረው እና ዳንኤል ደርቤ በቀኝ በኩል በጥረቱ ገፍቶ ገብቶ ከርቀት የመታት እና በግቡ ቋሚ ስር ሾልካ የወጣችበት ሀዋሳዎች ምላሽ ለመስጠት የተጣጣሩባቸው መልካም ዕድሎች ነበሩ፡፡
ሁለት ሙከራዎች በሀዋሳ ይስተናገድባቸው እንጂ የተሻሉ የነበሩት ፋሲሎች አጨዋወታቸውን ወደ ጎን ለጥጠው ሱራፌል እና በዛብህ በንክኪ የሚፈጥሩት አጋጣሚዎች ከፊት ለነበሩት ሁለቱ አጥቂዎች ሙጂብ እና ኢዙ ቶሎ ቶሎ ለማድረስ ጥረቶች አልተለዩዋቸውም፡፡ በዚህም ሂደት ሁለተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል፡፡ 15ኛው ደቂቃ ላይ በሜዳው የግራ አቅጣጫ ከሀዋሳ የግብ ክልል በራቀ ቦታ ላይ ተስፋዬ መላኩ በኢዙ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በማይታመን ቅፅበት የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ሀብቴ ከድር ባጠበበት አቅጣጫ ማራኪ ጎል አስቆጥሮ የዐፄዎቹን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡
ሁለት ለምንም መመራት የጀመሩት ሀይቆቹ ከደጋፊዎቹ ጠንካራ ተቃውሞን አስተናግደዋል፡፡ የክለቡ ደጋፊዎችም የአሰልጣኝ አዱሴ ካሳን ስም እየጠሩ ተቃሞ ያቀረቡ ሲሆን ግብ ጠባቂው ቢሊንጌ ኢኖህም በተመሳሳይ ክለቡን ይልቀቅ እያሉ በፅሁፍም ጭምር ተቃውሞን ሲያስተጋቡ ተስተውሏል። አንድዳንድ ደጋፊዎችም የውሀ ፕላስቲክ በአሰልጣኙ ላይ ወርውረዋል፡፡
በፋሲል ከተማ ለመበለጥ ተገደው የነበሩት ባለሜዳዎቹ በፍጥነት እጅግ አስገራሚ እንስቃሴን አድርገው ወደ ጨዋታ ተመልሰዋል፡፡ ዐፄዎቹም ሁለት ግብ ማስቆጠራቸው ጨዋታውን የጨረሱ አስመስሏቸው ወርደው ለመበለጥ ተገደዋል፡፡ የሀዋሳን ተሻጋሪ እና የመልሶ ማጥቃትን እንቅስቃሴ መቋቋም ያቃተው የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቡድን ሦስት ተከታታይ ጎሎችን በመጀመርያው አጋማሽ ለማስተናገድ ተገዷል፡፡በቀኝ በኩል ተከላካዮችን እየረበሸ ሰብሮ ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረትን ሲያደርግ የዋለው መስፍን ታፈሰ ወደ ግቡ በግራ እግሩ ሲልክ ዳንኤል ደርቤ ደርሶ በቀጥታ መትቶ ሳማኬ ሚኬል አድኖበታል፡፡ አሁንም ግብ ለማስቆጠር የፋሲል ግብ ክልል ሲያነፈንፉ የነበሩት ሀዋሳዎች ግብ አግኝተዋል፡፡ 20ኛው ደቂቃ ላይ ከወትሮ ደካማ አቋሙ የነቃ የሚመስለው ዳንኤል ደርቤ በግራ በኩል ሰይድ ሀሰንን አልፎ ያሻገረውን ኳስ ልማደኛው አጥቂ ብሩክ በየነ ወደ ጎልነት ቀይሯት ሀዋሳን ወደ 2ለ1 ቀይሯል፡፡
የፋሲል ከነማን በሒደት መዳከም የተመለከቱት ሀዋሳዎች ድክመታቸውን ተጠቅመው አቻ ሆነዋል፡፡ 23ኛው ደቂቃ ላይ ለሀዋሳ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ጉልህ ሚና የነበረው ዳንኤል ደርቤ በቀኝ በኩል እየነዳ መቶ መሬት ለመሬት የሰጠውን ኳስ አማካዩ ሄኖክ ድልቢ ከሳጥን ውጪ እጅግ ማራኪ ግብ ሚካኤል ሳማኪ መረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን 2ለ2 አድርጓል፡፡ አሁንም ለማጥቃት ያልቦዘኑት ሀዋሳዎች ሶስተኛ ግባቸውን በእጃቸው አስገብተዋል፡፡ 34ኛው ደቂቃ ዘላለም ኢሳያስ ከማዕዘን ሲያሻማ ተስፋዬ መላኩ በግንባር አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በጉዳት ለሀዋሳ ግልጋሎተት ሳይሰጥ የከረመው መስፍን ታፈሰ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሯል፡፡ ይህች ግብ ስትቆጠር የፋሲል ከነማ ግብ ጠባቂ ሚካኤል ሳማኬ እና ተከላካዮች የሰሩት የአቋቋም ስህተት በግልፅ የታየበት ነበር።
ከእረፍት መልስ ፋሲል ከነማዎች ኳስን በመቆጣጠር ከሀይቆቹ የተሻሉ ሲሆኑ ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ግን ተመሳሳይ መልክን ሁለቱም ተከትለዋል፡፡ ከርቀት የሚመቱ ኳሶች የበዙበት ሁለተኛው አጋማሽ በተለይ ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት ሲመታቸው የነበሩት ጠንካራ ኳሶች ለሀዋሳው ግብ ጠባቂ ፈታኞች ነበሩ፡፡ 51ኛው ደቂቃ ሀዋሳዎች የፈጠሩት የግብ ሙከራ በዚህኛው አጋማሽ ቀዳሚዎቹ ምካሪዎች አድርጓቸዋል፡፡ በቀኝ በኩል መስፍን ታፈሰ በረጅሙ ወደ ግብ ሲያሻማ ብሩክ በየነ በግንባር ገጭቶ በላይኛው ብረት ታኮ የወጣበት አስቆጪ ሙከራ ነበር፡፡ ፋሲሎች በማጥቃቱ የተዋጣላቸው ቢሆኑም ጠንካራውን የሀዋሳ የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት በደንብ ተቸግረዋል በተለይ ለዚህ ተጠቃሹ የሀዋሳው ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ድርሻ የማይናቅ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለፋሲል እንቅስቃሴ ማማር የራሱን ድርሻ ሲያበረክት የነበረው ኢዙ አዙካ ተቀይሮ ከወጣ በኃላ በእንቅስቃሴ ቡድኑ ይሻል እንጂ ወደ ግብ የመድረሱ አብዛኛዎቹ ስራዎች ሱራፌል ላይ በዝተዋል፡፡
ሱራፌል ዳኛቸው ተደጋጋሚ ያደረጋቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ጠንካራ የርቀት ኳሶች ምናልባት ዐፄዎቹን ወደ ጨዋታ ሊመልሱ ሚችሉ ቢሆኑም ባክነዋል፡፡ በተለይ ሱራፌል ሁለቴ ገፋ አድርጎ ወደ ሳጥን ከተጠጋ በኃላ ወደ ግብ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር የመለሰበት አጋጣሚ አስቆጪዋ ዕድል ነበረች፡፡ ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እንየው ካሳሁን እና ዓለምብርሀን ይግዛውን ለውጠው ካስገቡ በኃላ ረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች ላይ አትኩረው ታይተዋል፡፡ 83ኛው ደቂቃ አለምብርሀን በቀኝ በኩል አሻምቶ ቆሞ የዋለው ሙጂብ ቃሲም በግንባር ገጭቶ ለጥቂት የወጣችበት እንዲሁም ዓለምብርሀን ራሱ መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎ ወደ ውጪ የወጣበት ሂደትን ፋሲሎችን በስተመጨረሻ ወደ ግብ አቅርቧቸው ነበር፡፡
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጭማሪ ላይ ብሩክ በየነ በቀኝ በኩል ያገኛትን ኳስ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶ ሳማኪ እና የግቡ ብረት ተባብረው ወደ ውጪ ያወጧት የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ አራት የምታሳድግ የነበረች ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች በሀዋሳ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ